
ደሴ: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዲኤምቪ ፎር ደሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት የረመዳን እና ዐቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ አድርጓል። ድርጅቱ ከ900ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 500 የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው የዱቄት እና የዘይት ድጋፍ ያደረገው።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ አሚናት አሊ የጤና እክል እንዳለባቸው ገልጸዋል። ዲኤምቪ ፎር ደሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት በየወሩ 1ሺህ 5ዐዐ ብር እንደሚሰጣቸው እና ዛሬም በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። ሌላዋ እናት ወይዘሮ ሙሉ ገበየሁ ድርጅቱ በየወሩ ከሚያደርግላቸው የ1ሺህ 500 ብር ድጋፍ በተጨማሪ በበዓላት ጊዜም ድጋፎችን እንደሚያደርግላቸው ነው የተናገሩት።
በድጋፉ ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ዲኤምቪ ፎር ደሴ በተለያዩ ጊዜያት እያደረገ ያለው ድጋፍ ሰፊ እና የሚያሥመሠግን መኾኑንም ገልጸዋል። በዚህ የጾም ወቅት እንዲህ አይነት የበጎ ፈቃድ ድጋፍ በፈጣሪም በሰዎችም የተወደደ መኾኑን አንስተዋል።
እንዲህ አይነቱ ተግባር መንግሥት ሊሸፍነው ያልቻለውን ወጭ በመሸፈን የማኅበረሰቡን ችግር የሚያቃልል በመኾኑ ሊበረታታ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከተቋቋመት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ100 አረጋውያን በቋሚነት ድጋፍ እያደረገ ነው።
ድርጅቱ 64 ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ታዳጊዎች ለእያንዳንዳቸው በዓመት 20ሺህ ብር፤ ለ34 የካንሰር ታማሚዎች በየወሩ 1ሺህ 500 ብር፣ ለስድስት የኦቲዝም ችግር ላለባቸው ሕጻናት በቋሚነት ድጋፍ ከማድረግ አልፎ በከተማው የሚገኘውን የረዋን የኦቲዝም ማዕከልን ገንብቶ ለከተማ አሥተዳደሩ ማስረከቡ ተገልጿል።
በቀጣይ ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመነጋገር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የድርጅቱ አማካሪ ማዘንጊያ አበበ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ሙሀመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!