የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ተጠናቅቆ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት መጀመሩን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

28

ደሴ: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የመጀመሪያው ዙር 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ተጠናቅቆ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት መጀመሩን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገልጿል። የተጀመረው የኮሪደር ልማት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የኮሪደር ልማቱ በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መኾኑንም መምሪያው ገልጿል። በኮምቦልቻ ከተማ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለማከናወን ታስቦ ነው ወደ ሥራ የተገባው። በበጀት ዓመቱም 5 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ሲሳይ አየለ በመጀመሪያው ዙር 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በማጠናቀቅ እና ክፍት በማድረግ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት መጀመሩን ገልጸዋል። ለኮሪደር ልማቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው በቀጣይም ይህ በጎ ተግባር መጠናከር አለበት ብለዋል።

ልማቱ በራስ በጀት የሚከናወን እንደመኾኑ በጀት ፈተና እንደነበርም ጠቁመዋል። ፈተናውን ግን በኅብረተሰቡ ተባባሪነት መፍታት መቻሉንም አስገንዝበዋል። ልማቱ በራስ አቅም እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው ወጭን በመቆጠብ በጥራት እና በጊዜ ለማከናወን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም በማጠናቀቅ የበጀት ዓመቱን የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ዕቅድ እንደሚያሳኩ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ባሉ ቀበሌዎች እና ክፍለከተማዎች ኅብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎችን እያነሳ ነው ያሉት ኀላፊው በተለመደው የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና ቀና ትብብርም ልማቱ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በቀጣይ ልማቱን በማጠናከር የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ይሠራል ብለዋል። የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውብ ገጽታ ከመጨመር ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ እና የሥራ ባሕልን የቀየረ መኾኑንም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡- ኃይሉ መላክ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ መማሪያ ክፍሎች ተመረቁ።
Next articleዲኤምቪ ፎር ደሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ።