“የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የጣና ሐይቅን የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

64

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የባሕር ዳር ከተማን የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ጣና ሐይቅን የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ ከጣና የሚመጣውን ነፋስ በደንብ እንዲያገኘው የሚያደርግ፣ ጣናንም በደንብ የሚገልጥ መኾኑን ነው የተናገሩት። በጣና ሐይቅ ዙሪያ ምቹ የኾነ ነገር እየተገነባ መኾኑንም ገልጸዋል። የባሕር ዳር እንቅስቃሴ ሰላማዊ መኾኑንም ተናግረዋል። በባሕር ዳር ከተማ አዳዲስ የመዝናኛ ፕሮጄክቶች እየወጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ስታዲዬም ውብ ኾኖ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ስታዲዬሙ የካፍ እና የፊፋን ደረጃ በሚያሟላ መልኩ ደረጃን ጠብቆ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በልዩ ጥንቃቄ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል። ኢትዮጵያ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠየቀችው ጥያቄ ምላሽ ካገኘ ባሕር ዳር አንደኛው የማጫወቻ ሜዳ እንደሚኾን ነው የተናገሩት።

የባሕር ዳር ስታዲዬም ሌሎች የዓለም ሀገራት የእግር ኳስ ቡድኖች እና የብሔራዊ ቡድኖች በሀገራቸው ለእግር ኳስ የተመቻቸ ወቅት በማይኖሩበት ጉዜ መጥተው እንዲጫወቱበት ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል። ስታዲዬሙ ከ80 በላይ ሱቆች፣ ከአሥራ አንድ በላይ ካፌና ሬስቶራንቶች ያሉት መኾኑንም አንስተዋል። ስታዲዬሙ ኳስ ለመጫዎቻ ብቻ ሳይኾን ለቱሪዝም መዳረሻ የሚኾን መኾኑንም ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ዙሪያ የጭስ ዓባይ፣ የዘጌ እና ሌሎች በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የጎርጎራ እና የጎንደር አብያተ መንግሥትን ከባሕር ዳር ቱሪዝም ጋር ማስተሳሰር እንደሚቻልም ገልጸዋል። ባሕር ዳር ከተማ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚንቀሳቀሱ ጎብኝዎች ማረፊያ እንደምትኾንም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ለየት የሚያደርገው በችግርም ውስጥ ኾኖ ማልማት እንደሚቻል ማሳያ መኾኑ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ መማሪያ ክፍሎች ተመረቁ።