“የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ለየት የሚያደርገው በችግርም ውስጥ ኾኖ ማልማት እንደሚቻል ማሳያ መኾኑ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

81

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የባሕር ዳርን የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባሕር ዳር በተፈጥሮ የታደለች ውብ ከተማ ናት፣ የአየር ንብረቷም የተመቸ ነው ብለዋል። በከተማዋ ሰፊ የኾነ የእግረኛ መንገድ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በባሕር ዳር የተሠራው ልዩው ነገር ለነዋሪዎች ዝግ የነበረውን የጣና ሐይቅን የሚከፍት ውብ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የጣና ሐይቅ ዙሪያ ሥራ ሰው በስፋት የሚይዝናናበት ኾኖ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት እና የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሲገናኙ የሀገርን ውበት ይገልጣሉ ብለዋል። ጎንደር ላይ ከፒያሳ እስከ ኤርፖርት ድረስ የኮሪደር ልማት ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርፖርት ጎርጎራ ቅርብ ነው፣ ጎርጎራም ውብ ኾኖ ተሠርቷል፣ ጎርጎራ ከባሕር ዳር ጋር ሲተሳሰር ደግሞ ድንቅ ይኾናል ነው ያሉት።

“የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ለየት የሚያደርገው በችግርም ኾኖ ማልማት እንደሚቻል ማሳያ መኾኑ ነው” የባሕር ዳር ልማት በችግርም ውስጥ ኾኖ ሕልም ካለ፣ ትጋት ካለ፣ ከባቢ መለወጥ፣ ልማት ማምጣት እንደሚቻል የሚያመላክት ነው” ብለዋል።

የጣና ሐይቅ ዙሪያ የብዙ ሰዎች መዝናኛ መኾን መቻል እንዳለበትም ተናግረዋል። በከተማዋ አዳዲስ የመዝናኛ ቦታዎች እየወጡ መኾናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሕር ዳር ውበቷ አድጎ፣ ውበቷ ወደ ገንዘብ እንዲቀየር፣ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝቡ በጀመሩት መንገድ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት የመሪ ራዕይ እና ጥበብ ያሳየ መኾኑን ተናግረዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከጽሕፈት ቤታቸው ጀምረው የልማት ሥራዎችን መሥራታቸውንም አንስተዋል። ባሕር ዳር ላይ አሁን በተጀመረው መንገድ ዓመት ሁለት ዓመት ብንሠራ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በአፍሪካም ውብ የኾነች ከተማን መሥራት እንችላለንን ነው ያሉት።

የተጀመረውን ሥራ ጥንቅቅ ማድረግ፣ ድልድዩን ከውኃው፣ ውኃውን ከሆቴሉ ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል። ባሕር ዳር ለስፖርት፣ ለቱሪዝም፣ ለኮንፈረንስ ከበቂ በላይ ማዕከል ትኾናለች ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት ማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል” አሕመዲን መሐመድ ( ዶ.ር)
Next article“የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የጣና ሐይቅን የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ