
አዲስ አበባ: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የልማት ተነሺ ባለይዞታዎችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም የሚያስችል የውይይት መድረክ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሠይፈ ሠይድ መሬት የሕዝብ እና የመንግሥት የጋራ ሀብት በመኾኑ ለልማት መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ መኖሩን አንስተዋል።
በክልሉ ከ2012 እስከ 2016 ባሉት ዓመታትም ከ29 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለልማት መወሰዱን ገልጸዋል። የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት ማቋቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጫና እየፈጠረ በመምጣቱ የክልሉ መንግሥት ለመሬት ቢሮው በጀት በመመደብ እልባት ለመስጠት እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ ( ዶ.ር) ባለፉት አምስት ዓመታት 166 ሺህ በላይ ባለይዞታዎች ለልማት መነሳታቸውን ገልጸዋል። ለልማት ከተነሱ ወገኖች መካከል 31 በመቶ የሚኾኑትን የልማት ተነሺዎች ብቻ በዘላቂነት ማቋቋም መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም የልማት ተነሺዎችን ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ውስብስብ ችግሮች አጋልጧቸዋል ነው ያሉት። “ክልሉ ካሉት ፀጋዎች መካከል መሬት አንዱ በመኾኑ በአግባቡ ማልማት እና የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት ማቋቋም በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው” ብለዋል። ለዚህም የሚመለከታቸው እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እና በኀላፊነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እና የልማት ተነሺ ተወካዮች ተሳታፊ ናቸው።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን