“የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት የተሻለ የፍትሕ አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት ተልዕኮ ይዞ ተደራጅቷል” አቶ ዓለምአንተ አግደው

28

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ለተቋቋመው የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት የሥራ ማስጀመሪያ የትውውቅ መድረክ አካሂዷል። በትውውቅ መድረኩ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሠብሣቢ ዓለምአንተ አግደውን ጨምሮ ሌሎች የቦርዱ አባላት፣ የፍትሕ ተቋማት መሪዎች እና የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ አበራ ኢንስቲትዩቱ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ ሥራ እና አጫጭር ሥልጠናዎች በመስጠት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የሕግ ጥናት እና ምርምር ሥራን በመጨመር እየሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱን የበለጠ ለማጠናከር ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲኾን በአዋጅ መሰየሙን ጠቅሰው የተሻለ የአቅም ግንባታ እና የምርምር ሥራ ለመሥራት ሰፊ ዕድል እንደተፈጠረለትም ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ኢንስቲትዩቱን የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት መደበኛ ጉባኤው በአዋጅ አሻሽሎ ማቋቋሙን ገልጸዋል። የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱ በትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ነው ያሉት ዶክተር ደሴ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥም አንዱ የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን ሥርዓቱን ተቋማዊ ለማድረግ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩቱን እንደገና ለማደራጀች የተሠራውን ሥራ ጠቅሰዋል።

የፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ዋናው የሰው ኀይል ልማት መኾኑ ታምኖበት የነበሩ የአደረጃጀት እና የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ እና ተመክሮበት በምክር ቤት እንዲጸድቅ መደረጉንም አስታውሰዋል። ለዚህም የቦርድ ሠብሣቢው ላደረጉት ጥረት አመሥግነዋል።

በቀጣይም የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በቦርድ አመራሩ የሚሰጠውን መመሪያ እና አቅጣጫ በመከተል ከሠራተኞች እና ከክልሉ መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሰጠንን ተልዕኮ እንወጣለን ብለዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሠብሣቢ ዓለምአንተ አግደው የኢንስቲትዩቱን አዲስ መሪዎች እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለዋል።

የቦርድ ሠብሣቢው በሰጡት የሥራ መመሪያም ኢንስቲትዩቱ ቀድሞ የተደራጀ ቢኾንም ገለልተኛ እና ነጻ ኾኖ ብቁ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ባለሙያዎችን ለማፍራት እና አቅም ለመገንባት ተልዕኮ መሰጠቱን ገልጸዋል። የፍትሕ እና የዳኝነት አገልግሎትን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በምርምር በመፍታት የተሻለ የፍትሕ አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት ተልዕኮ ይዞ መደራጀቱንም አንስተዋል።

ተቋሙ በክልል ደረጃ ለፍርድ ቤት፣ ለዐቃቢ ሕግ፣ ለፖሊስ እና ለሌሎች የፍትሕ አካላት የጀርባ አጥንት ኾኖ የሚሠራ ከፍተኛ ተልዕኮ ያለው መኾኑንም ጠቅሰዋል። በክልል በሚነሱ የሕግ ጉዳዮች ላይም ጥናት እና ምርምር በማድረግ የችግሮችን መንስኤ በመለየት መፍትሄ የሚኾኑ ውጤታማ ሥራዎች እንደሚሠራ ይጠበቃል ብለዋል።

የሥራ አመራር ቦርዱም ኢንስቲትዩቱ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እና ሠራተኞች ተቋማቸው ኀላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ ቀዳሚ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አደራ ብለዋል።

የቦርድ ሠብሣቢው ኢንስቲትዩቱ እንደገና እንዲደራጅ ሙያዊ እና አሥተዳደራዊ ኀላፊነታቸውን የተወጡ እና ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመሥግነዋል። ለተሾሙት የኢንስቲትዩቱ መሪዎች፣ ለሠራተኞቹ እና ለሥራ አመራር ቦርድ አባላት መልካም የሥራ ጊዜንም ተመኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ንጋት ኮርፖሬት የክልሉ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ እየተጋ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleበሰላም፣ ልማት እና መልካም አሥተዳድር ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።