
አዲስ አበባ: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ንጋት ኮርፖሬት በፈረንጆቹ 2024 ስኬታማ አንዲሆኾን ላደረጉ የተቋሙ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ ዓድዋ ሙዚየም ዕውቅና ሰጥቷል።
በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ንግግር አድርገዋል። እንደ ንጋት ኮርፖሬት አይነት ተቋማት የክልሉን አቅም በማሥተባበር እና በማልማት ያላቸው ሚና ትልቅ ነው ብለዋል።
ንጋት ኮርፖሬት የክልሉ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ እየተጋ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ክልሉ ቀውስ ሲያጋጥመው ፈጥኖ በመድረስ በትምህርት፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲሁም ከቁስ እስከ ሰብዓዊ መስዋዕትነት መክፈል ድረስ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሮቻችን ማዳበሪያ እንዲደርሳቸው በማድረግም ያከናወነውን ድጋፍ እና መስዋዕትነት የክልሉ መንግሥት እንደማይዘነጋው አውስተዋል።
የእርሻ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ማዘመን እና አግሮ ፕሮሰሲንግን ማበልጸግ ትልቁ ተልዕኮ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን የመሬት አቅርቦት አንደሚያዘጋጅ ቃል ገብተዋል።
የላቀ አፈጻጸም ላመጡ ተቋማት አንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከዚህ በተሻለ ለመተግበር አንዲተጉ እና ትርፍን መሠረት አድርገው እንዲጥሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የንጋት ኮርፖሬት ቦርድ ሰብሳቢ እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ስዩም መኮንን ንጋት ኮርፖሬት ባለፈው አንድ ዓመት 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያተረፈ ሲኾን ከትርፍ ባሻገር በማኅበራዊ ኀላፊነት ሥራ ማለትም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በትምህርት እና ስፖርት ማሳደግ ዘርፎች ሚናውን ተወጥቷል ብለዋል።
የቀውስ ወቅት አመራርን በመከተል የጸጥታ ተጽዕኖውን የከፋ ችግር መቀነስ ችሏል ነው ያሉት።
ኮርፖሬቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 9 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያሳየ ሲኾን በአክሲዮን ከያዛቸው ተቋማት 31 በመቶ እና በባለቤትነት ከሚያሥተዳድራቸው ደግሞ 69 በመቶ ትርፍ መገኘቱን ገልጸዋል። ለመንግሥት ግብር ብቻ በዓመቱ 531 ሚሊዮን ብር ከፍሏል ነው ያሉት።
ንጋት ከተወሳሰቡ አሠራሮች እና አደረጃጀቶች በመውጣት በተሻለ ትርፋማነት እና የልማት መሠረት እያረጋገጠ ይቀጥላል ብለዋል።
የንጋት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ባምላኩ አስረስ (ዶ.ር) በሀገራችን ያለው አለመረጋጋት እና የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካ በኮርፖሬቱ ንግድ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት 11 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረግ መቻሉን ያነሱት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ንጋት በመልቲሞዳል ኦፕሬተርነት ለመሰማራት ፈቃድ ያገኘ ነው ብለዋል።
በጥቁር አባይ እና በከልቻ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በሀገሪቱ ቀዳሚ አቅም ያለው ተቋም ለመኾን ችሏል ነው ያሉት።
ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት አለን ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ እድገት አለውም ብለዋል።
ተቋማቱ በተለያዬ መስፈርት የተሸለሙ ሲኾን አምባሰል ንግድ ሥራዎች እና ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ የ2025 ሞደል የኤሌክትሪክ መኪና ተሸልመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!