“አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

18

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያሳልጡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አሕጉራዊ የፋይናንስ እና ምጣኔ ሀብት የሚኒስትሮች ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዬሱፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ፣ የአፍሪካ አሕጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ እና የዚምባቡዌ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ልማት እና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ እና ተሰናባቹ የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ እና ልማት ሚኒስትሮች ቢሮ ሊቀመንበር አንድሪው ቡቩምቤ ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት” አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች” ብለዋል። የአፍሪካን ድንበር የለሽ ነጻ የሸቀጥ እና የአገልግሎት ግብይት መሻት ተስፋን እውን ለማድረግ ከምኞት የዘለለ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለረጅም ጊዜያት የአፍሪካ የንግድ ሥርዓት እንቅፋት የኾኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ተጨባጭ እርምጃ እና ስትራቴጂካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህም ሀገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ከማጽደቅ ባለፈ ወደ ተግባር መለወጥ እና ስኬታማ ብሔራዊ የትብብር ኮሚቴ አዋቅሮ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ እሴት የተጨመረበት ምርታማነት፣ የፓን አፍሪካ ምርምር ዕድገት፣ ግልጽና ተገማች የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። በጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ዕድገት፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎ እና አሕጉራዊ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት አቅም ማጎልበት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የንግድ ውህደት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኑን አስታውቀዋል። ለአብነትም የኢትዮ-ጅቡቲን የሚያስተሳስር የምድር ባቡር መስመር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም እና የውኃ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ምሳሌ መኾናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኛትን የድንበር ተሻጋሪ ኮሪደር፣ የንግድና ትራንስፖርት መንገድ መሠረተ ልማት ግንባታም ለአፍሪካ አሕጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ አቅም የሚኾን ተመጣጣኝ፣ ታዳሽ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ እየሠራች ትገኛለች ሲሉም ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርክ እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራዎችም ለአፍሪካ አሕጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራ ያላትን ዝግጁነት የሚያመላክቱ መኾናቸውን አንስተዋል። በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባዔ “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤ አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” በሚል መሪ መልዕክት መካሄዱን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሴቶች ሲለወጡ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ
Next article“ንጋት ኮርፖሬት የክልሉ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ እየተጋ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ