“ሴቶች ሲለወጡ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ

23

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በንቅናቄ የተሠሩ ተግባራትን ከሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ገምግሟል። በቢሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በንቅናቄ የተሠሩ ተግባራትን የሚያመላክት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን እንደ ቢሮ ከየካቲት 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም አካባቢ በንቅናቄ አክብረናል ብለዋል። በዚህም ብዙ ተግባራት ተሠርተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የበዓሉ ዓላማ በሴቶች ላይ የሚደረሰውን ጫና በመቀነስ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ያለመ ሲኾን ሴቶች ችግራቸውን በተናጠል መታገል ስለማይችሉ ራሳቸውን በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተለይ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋልም ብለዋል።

“ሴቶች ሲለወጡ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ያሉት ኀላፊዋ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ከገጠር እስከ ከተማ የሚገኙ ሴቶች የሌማት ትሩፋትን በየጓሯቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማድረግ የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሴቶች ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ እንዲያገኙም በቢሮው በኩል ትልቅ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ሌላው እና በዚህ ዓመት በጣም አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የሴቶች የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል በትኩረት ተሠርቷል። በሽታው በጣም አስጊ በመኾኑ የመከላከል ሥራው በንቅናቄ እንዲሠራ የተደረገ ሲኾን ይህም እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል ብለዋል። ኀላፊዋ ይህ ሁሉ ውጤታማ እንዲኾን ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በበኩላቸው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ በንቅናቄ የተሠራው ሥራ በጣም የሚበረታታ እንደነበር ገልጸው ሴቶች በዶሮ ርባታ፣ በጓሮ አትክልት፣ በእንስሳት እርባታ እና በልዩ ልዩ የሌማት ትሩፋት ዘርፎች በሀገር ደረጃ ሞዴል የሚኾን ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።

ለዚህም ማሳያ በክልላችን በሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ ሴቶች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል። ይህንን አስመልክቶም እንደ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን በከፍተኛ ሁኔታ የሚዲያ ሽፋን በመስጠታችን ተግባሮቻቸውን ወደ ሁሉም አካባቢ ተደራሽ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉን ዶክተር መንገሻ ተናግረዋል። ለዚህም ለሁሉም የሚዲያ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የሴቶች ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመኾኑ ጉዳያቸውን የእለት ከእለት ተግባር በማድረግ ከንግግር ባለፈ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ሁለንተናዊ ችግሮችን በተግባር መሥራት እና መታገል ይጠበቅብናልም ነው ያሉት።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በነበረው ንቅናቄ የሴቶችን ተሳትፎ ሊያበረታቱ የሚችሉ በተለይም በሁሉም የልማት እንቅስቃሴዎች በሴቶች የተሠሩ ተግባራትን በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ወደ ሁሉም አካባቢ ተደራሽ እንዲኾኑ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደተወጣ ተናግረዋል።

በሁሉም ነገር ሴቶችን አካቶ መስራት በጣም አስፈላጊ መኾኑንም ነው ተሳታፊዎቹ የገለጹት፣ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንደዘገበው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት በጥራት እና በፍጥነት እየተከናወነ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ