
ደሴ: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌይማን እሸቱን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች የደሴ ከተማን የኮሪደር ልማት የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌይማን እሸቱ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በአጠቃላይ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በፍጥነት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
የከተማውን ሕዝብ በማስተባበር እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር አፈጻጸሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማቱ ሊያሟላቸው የሚገቡ ሁሉንም መስፈርቶች እየተሠሩ እንደኾነም ጠቅሰዋል። ማኅብረሰቡ ለልማቱ ያሳየው ድጋፍ የሚበረታታ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኀላፊው ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቃሲም አበራ በከተማዋ ኅዳር 10/2017 ዓ.ም የተጀመረው የኮሪደር ልማት ጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ከቧንቧ ውኃ እስከ አቡኑ ግቢ ድረስ ያለው መንገድ የአስፋልት ንጣፍ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል። ቀሪ ሥራዎችንም በሁለት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!