የተዘነጋው ኤች አይ ቪ ኤድስ!

27

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የነጋገርናቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ኤች አይ ቪ የፈጠራ ወሬ እንጅ በበሽታ አይደለም የሚል አቋም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከመጠንቀቅ ይልቅ በተደጋጋሚ ለኤች አይ ቪ በሚያጋልጥ መንገድ መቆየታቸውን ነግረውናል፡፡ በሂደትም የኤች አይ ቪ ተጠቂ መኾናቸውን ስለማወቃቸው አጫውተውናል።

“በመዘናጋቴ የኤች አይ ቪ ኤዲስ ተጠቂ ኾንኩ” የሚሉት ሀሳብ ሰጭው ወጣቱ ከእኔ ትምህርት ቀስሞ ጤናውን በአግባቡ እንዲጠብቅ መክረዋል። ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪም አሁን ላይ በተማሪዎች ዘንድ መዘናጋት መኖሩን ታዝቢያለሁ አለን፡፡ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የሚለቀቁ ወሲብ ቀስቃሽ ጽሑፎች፣ ምስሎች እና ፊልሞች ወጣቱን ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ እንዳደረጉት ገልጿል።

አኹን ላይ የኮንዶም እጥረት መከሰቱ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል፤ ስለዚህ መንግሥት ሊያስብበት ይገባዋል“ ነው ያለው፡፡ ለኤች አይቪ አጋላጭ በኾነ ሥራ መቆየታየውን የነገሩን ወይዘሮ ደግሞ ወደሳቸው የሚመጡትን ደንበኞች ኮንዶም እንዲጠቀሙ ይመክሩ እንደነበርም ነው ያብራሩት፡፡

አንዳንዶች ፈቃደኛ ሲኾኑ ፈቃደኛ የማይኾኑትን እንደማያስተናግዷቸው ተናግረዋል፤ ይሁንና ፈቃደኛ ከኾኑ በኋላ የሚዘናጉ እና በሕይዎታቸው ላይ አደጋ የሚጋብዙም ያስተውሉ እንደነበርም ነው የጠቆሙት፡፡ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመው ቀደም ሲል በዘመቻ እና ንቅናቄ መልክ ኹሉንም የኅብረተሰብ ክፍል መሠረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አኹንም ቢሮው ይበልጥ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተስብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። ዳይሬክተሩ በአማራ ክልል ወጣቱ ስለ ኤች አይቪ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነሱ አኹን ስርጭቱ እየጨመረ ነው ብለዋል።
የኮንዶም እጥረት ማጋጠሙ ደግሞ ለበሽታው መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት መኾኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ ለኮንዶም መግዣ ተብሎ በጀት አይያዝም ያሉት ዳይሬክተሩ ከፌዴራል የሚላከውም አነስተኛ ነው ብለዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ወጣቶች በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ለምሳሌ በወጣት ማዕከላት አካባቢ የኮንዶም አቅርቦቱ እና ስርጭቱ ከፍተኛ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ አኹን ግን ይህ የኮንዶም አቅርቦት በመቅረቱ ወጣቱ በከፍተኛ ኹኔታ በአዲስ በኤች አይ ቪ እንዲያዝ አድርጓታል ነው ያሉት።

በየደረጃው ያሉት መሪዎች ለኤች አይ ቪ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሥራውን እየገመገሙ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ኮንዶምን በተመለከተ አቅርቦቱን እና ስርጭቱን ተደራሽ ለማድረግ በጀት መመደብ እንደሚገባው እና ማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል በተለይ ወጣቱ ለአፍታም ቢኾን መዘናጋት እንደሌለበት አቶ ውድነህ ተናግረዋል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሌማት ትሩፋት ሥራ አዋጭ መኾኑን ወጣቶች ተናገሩ።
Next article” በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው በሕዝቦች የነቃ ተሳትፎ መኾኑን ፓርቲው በፅኑ ያምናል” ብልጽግና ፓርቲ