የሌማት ትሩፋት ሥራ አዋጭ መኾኑን ወጣቶች ተናገሩ።

23

እንጅባራ: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የሌማት ትሩፋት ሥራ አዋጭ መኾኑን በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ተናግረዋል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጓንጓ ወረዳ እና ቻግኒ ከተማ አሥተዳደር በሌማት ትሩፋት ሥራዎች ላይ በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው ራሳቸውን እየለወጡ ነው። የሌማት ትሩፋት ሥራቸው ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ ሊኾን የሚችል ነው ።

የክልሉ፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች በቻግኒ ከተማ በመገኘት በከብት ማድለብ እና በወተት ላሞች ርባታ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን የሥራ እንቅሰቃሴ ተመልክተዋል፡፡ ሥራዎቻቸው በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመጎበኘቱ ለቀጣይ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ወጣቶች ተናግረዋል፡፡በሌማት ትሩፋት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች ሥራው አዋጪ መኾኑን ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሩ እና የገበያ ትስስር አለመኖር በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደኾነባቸው ገልጸዋል።

ለሥራው ውጤታማነት የሚያግዙ ሙያተኞች መኖራቸውን የተናገሩት ወጣቶቹ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ቶሎ ምላሽ አለመሰጠቱ የሥራውን ውጤታማነት እየፈተነው መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መኖ እና የብድር አቅርቦት ለማቅረብ ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ እና የእንስሳት እርባታ ተዋጽኦ ልማት ቡድን መሪ ምኒችል ተመስገን የተካሄደው ጉብኝት ከአልሚዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ከማገዝ ባለፈ ሥራው እንዲጠናከር ጉልበት የሚኾን ነው ብለዋል።

በገጠሩ እና በከተሞች የእንስሳት እርባታ እንዲስፋፋ እቅድ ተይዞ ሢሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም የእንስስት ዘርፍ ልማት ትልቅ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል። ለአልሚዎች ሙያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የብድር አቅርቦት ፣የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ወተት ልማት ላይ የተሰማሩትን በማኅበር እንዲደራጁ በማድረግ ወተት እየሰበሰቡ ለከተማው ማኅበረሰብ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወስዳው እንዲያሰረክቡ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ለቀጣይም በወተት ላይ እዬታየ ያለውን የገበያ ትስስር ችግር ለመፍታት እንሠራለን ብለዋል።

በማድለብ ሥታ የተሰማሩ ወጣቶች እስከ አዲስ አበባ ድረስ ይጭኑ እንደነበር የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መቆሙንም ተናግረዋል፡፡ የቦታ እና ሌሎች ተያያጅ ጥያቄዎችን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡-ሰሎሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
Next articleየተዘነጋው ኤች አይ ቪ ኤድስ!