
መጋቢት 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የማይካድራ ከተማ አሥተዳደር ለሚያከናውናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተደረገ የገቢ ማሠባሠቢያ መድረክ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ብር ተሰብስቧል።
በ2017 በጀት ዓመት “አንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት” በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ የሕዝብ ተሳትፎ በርካታ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት የማይካድራ ከተማ አሥተዳደርም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በራሱ በመመደብ ወደ ሥራ መግባቱን ከተማ አሥተዳድሩ አስታውቋል።
በከተማው የሚከናወኑት አጠቃላይ ፕሮጀክቶች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ በመኾናቸው እና በከተማ አሥተዳደሩ በጀት ለመሸፈን ስለማይቻል ሕዝቡን ያሳተፈ የገቢ ማሠባሠቢያ መርሐ ግብር በከተማ አሥተዳደሩ ተካሂዷል።
በአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት በሚል መልዕክት በብልጽግና ፓርቲ እና በመንግሥት በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ረገድ በዞኑ ከፍተኛ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ተናግረዋል።
ይህ ለውጥ እንዲመጣ ከፊት ቀድመው በመታገል ሕዝባቸውን ነጻ ያወጡትን መሪዎች እና ክቡር መስዋእትነት የከፈሉለትን ውድ ልጆቹን ፎቶ ግራፎች በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ ለጫራታ በማቅረብ ሕዝቡ እና ከተማ አሥተዳደሩ ለጀግኖቹ የሰጠውን ክብር አቶ ሲሳይ አድንቀዋል።
ማይካድራን ጨምሮ መላው ዞኑ ሰላሙን በራሱ አቅም አጽንቶ ልማቱንም በራሱ ክንድ እያረጋገጠ መኾኑንም አቶ ሲሳይ ጠቅሰዋል።
ትናንት ጀግኖቻችን መስዋእት ከፍለው ነጻ ወጥተናል ዛሬ ደግሞ እኛ ልማትን አጀንዳ አድርገን እየሠራን” ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።
አቶ አሸተ አክለውም የሰማዕታቱን ዋጋ እያስታወስን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ጠንክረን እየሠራን ነውም ብለዋል።
የማይካድራ ከተማ አሥተዳደር ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገዶችን እየገነባ መኾኑን የማይካድራ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይለፍ ዘውዱ ገልጸዋል።
አሥተዳደሩ በጀቱን በሕዝብ ተሳትፎ ለመደገፍ ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ በማዘጋጀት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አቶ ይለፍ አብራርተዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ያነሱት አቶ ይለፍ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል።
የማይካድራ ከተማ ልማት የተጀመረ እንጂ ያልተጠናቀቀ በመኾኑ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያለው ሀገር ወዳድ ሕዝብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!