“ወጣቶች ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ የስታርት አፕ ሥነ ምሕዳር ለመፍጠር ይሠራል” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የስታርት አፕ ውድድር ማጠቃለያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።

በማጠቃለያ መድረኩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በማጠቃለያ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)
ቴክኖሎጂን ለማልማት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ ኑሮን በማሻሻል፣ በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየሠራ ነው ብለዋል።

ከክልሎች እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የዛሬው መርሐ ግብር የመማሪያ ተሞክሮ፣ የፈጠራ ባሕል ማሳደጊያ፣ ሃሳባቸውን ወደ አዋጭ ንግዶች ለመቀየር የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ዓላማ ያዳረገ ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩ እንደ ሀገር እየተገነባ ያለው የስታርት አፕ ግንባታ ውስጥ መደላድል ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ነው የተናገሩት።

በመርሐ ግብሩ የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታቸውን፣ ጽናታቸውን እና የወደፊት ሕልማቸውን መገንዘባቸውም ገልጸዋል።

ያቀረቧቸው አዳዲስ ሃሳቦች እና መፍትሔዎች ተግዳሮቶችን የሚፈቱ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም ያላቸው የወደፊት ስታርት አፕ መሥራቾች መኾናቸውን አይተናል ነው ያሉት።

የፈጠራ ሃሳባቸውን እንደሚያሳኩም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የፈጠራ ውጤታቸውን ማሳደጋቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ፈጠራን ልምድ እንዲያደርጉም አሳሳስበዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመላው ኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ሥራ ፈጠራን ለመደገፍ እና ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ኾኖ እየሠራ ነው ብለዋል።

ወጣቶች ተሰጧቸውን እንዲያዳብሩ፣ ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ የስታርት አፕ ሥነ ምሕዳር ለመፍጠር መሥራታቸውን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

በመርሐ ግብሩ ለአሸናፊዎች ሽልማት እንደሚሰጥም ተናግረዋል። በኢኖቬሽን መርሕ የማያልቁ ዕድሎችን እንክፈት፣ እንጠቀምም ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈጠራን ማኅበረሰባዊ እና ተቋማዊ ባሕል ያደረጉ ሀገራት የሚገነቡት ኢኮኖሚ አይበገሬ ነው” አቶ አቤል ፈለቀ
Next articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ ነው።