
ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የስታርት አፕ ውድድር ማጠቃለያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በማጠቃለያ መድረኩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሰተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ የሀገር ሉዓላዊነት እና ጥንካሬ መመዘኛ መስፈርት ውስጥ አንዱ ኢኮኖሚ ነው ብለዋል። የኢኮኖሚ ዘርፉ ማኅበራዊ ባሕል እስኪኾን ድረስ ፈጠራን ታሳቢ ካላደረግን ብዙ ርቀት አንሄድም ነው ያሉት።
የሌላ ዓለም ግኝት የኾኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ከራስ ባሕል፣ እሴት፣ ታሪክ እና ማኅበራዊ መገለጫዎች ጋር አጣጥሞ ጥቅም ላይ ማዋል የፈጠራ ባሕልን ማኅበረሰባዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ የመጀመሪያው ሂደት ነው ብለዋል።
ፈጠራን ማኅበረሰባዊ እና ተቋማዊ ባሕል ያደረጉ ሀገራት የሚገነቡት ኢኮኖሚ አይበገሬ፣ በሁሉም ነገር የማይናወጥ እና የወደፊት ተራማጅ እንደሚኾን ተሞክሮ እያየን ነው ብለዋል።
ለብሔራዊ ጥቅም እና ፍላጎት ክፍተት እንዳይኖር ማኅበራዊ መሠረትን የማርቀቅ ግዴታ አለብን ነው ያሉት። የፈጠራ ሃሳብ ወደ መሬት ወርዶ ችግር ፈቺ፣ መወዳደሪያ አቅም እንዲኾን የተሰናሰለ እና የተሳለጠ አካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፈጠራ ሃሳቡ ወደ መሬት ወርዶ ጠንካራ አቅም እስኪፈጠር ድረስ የቅርብ ክትትል ያስፈልጋል ነው ያሉት። እንደ ክልል ሰፊ የፈጠራ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!