
ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት በ1844 ዓ.ም ነበር፡፡ ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ሸዋ ውስጥ ጎላ ወረዳ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው፡፡
14 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ከአባታቸው ጋር ከተቀመጡ በኋላ ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ) ጋር ተዋወቁ፡፡ የምኒልክ ባለሟል ኾነውም የተሰጣቸውን ሥራ ሁሉ በጥንቃቄ እና በብቃት እያከናወኑ ለመንግሥት ሥራ ታማኝ እና ትጉህ መኾናቸውን አስመሰከሩ፡፡
በፀባያቸውም ታጋሽ እና አስተዋይ ስለነበሩ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመኾን እንደ አባት እና ልጅ ይተያዩ ጀመር፡፡ በ1868 ዓ.ም በ24 ዓመታቸው የ”ባላምባራስ”ነት ማዕረግን ተሹመዋል፡፡
የሐረርጌን ግዛት በማቅናት እና በሚገባ በማሥተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ኾኑ፡፡ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለኾነው የ”ራስ” ማዕረግም በቁ፡፡
ልዑል ራስ መኮንን የአጼ ምኒልክ ተወካይ በመኾን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለአጼ ምኒልክም አሳውቀዋል።
የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲኾንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አሥተዳዳሪነት እና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጓቸው ያስቡ ነበር፡፡ ነገር ግን እምዬ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን በዚህ ሳምንት መጋቢት 1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
👉 የኢትዮጵያ የተውኔት ድርሰት
በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አስቀድሞ የተውኔት ድርሰት ስለመኖሩ የተጻፈ መረጃዎች አናገኝም። ይሁን እንጂ የቴአትር ትዕይንት ቀደም ብሎ እንደተጀመረ የሚያወሱ ድርሳናት አሉ።
ድራማዎቹ ይከወኑ የነበሩት ግን በድርሠት መልክ ተዘጋጅቶ እና እያንዳንዱ ተዋናይ የተሰጠውን ገጸ ባህሪ በጽሑፍ አጥንቶ ሳይኾን በቲያትሩሩ ደራሲ በቃል እየተመራና ተዋንያኑ የራሳቸውን ጥበብ ጨምረው ነበር ለመድረክ የሚቀርበው።
በ1913 ዓ.ም ገደማ ለህትመት የበቃውን ‹ፋቡላ የአውሬዎች ተረት› መጽሐፋቸውን ለቴአትር እንዲስማማ አድርገው በማቀናበር “ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያን” በሚል ርዕስ በሀገራችን የመጀመሪያው ሆቴል በኾነው ጣይቱ ሆቴል ለመድረክ የበቃው በዚህ ሳምንት ነበር።
ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያን የደረሱት በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተክለማርያም ናቸው፡፡
👉 የጨው ትግል
ማርች 12 ቀን 1930 ማህተማ ጋንዲ የጨው ሳቲያግራሃን (የጨው ትግል) የጀመሩት በዚህ ሳምንት ነበር። ይህ እንቅስቃሴ የሕንድ የነፃነት እንቅስቃሴ ወሳኝ አካል ነበር።
ሕንዳውያን ከእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። የቅኝ ግዛትን አምርረው ይታገሉ የነበሩት ማኅተመ ጋንዲ ሕንዳውያን የውጭ ወራሪዎችን እንዲታገሉ የማይተካ ሚና ነበራቸው።
ጋንዲ የትግላቸው መጀመሪያ የነበረውም በዚህ ሳምንት ለማታገያ ያነሱት የጨው ትግል ነበር። እንግሊዛውያን የሕንዳውያንን ሃብት በተለያየ መንገድ ይመዘብሩ ነበር።
ይህ የሀብት ምዝበራቸው እየተባባሰ ሲመጣ እና ሕንዳውያን ከሚጠብቁት በላይ ሲጎዱ ለመታገል ቆርጠው ተነስተዋል በመሪያቸው ማኅተመ ጋንዲ አማካኝነት።
በተለይም የጨው ምርቷን እያወጡ መልሰው ለሕንዳውያን ከፍ ባለ ዋጋ ይሸጡ የነበሩት እንግሊዛውያን ይህ ተግባራቸው በሕዝቡ ባለመወደዱ የነጻነት ችቦ ለማቀጣጠል ምክንያት ኾኗል።
ይህ ትግል በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ ሕንድ ከቅኝ ገዧ እንግሊዝ ለጻ ለመኾን በቅታለች። ኢንፎኔት ዶት ኮም የተሰኘ ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!