ትምህርት ቤቶችን መዝጋት የት ያደርሳል?

31

ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት የቀረው ግጭት የበርካታ ሰዎችን ሕይወዎት ቀጥፏል፡፡ የክልሉን ልማት ከማደናቀፉም በላይ የማኅበረሰቡን መስተጋብር አዛብቷል፡፡ ካስተጓጎላቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ትምህርት ነው።

እንደ አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ ዘንድሮ በክልሉ 4 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው አቋርጠዋል፡፡ በ2016 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩት በግጭቱ ምክንያት መምህራንም ለደህንነታቸው በመስጋት፣ ትምህርት ቤትም ባለመከፈቱ እና ወላጆች እና ተማሪዎችም ስለሚሰጉ ነበር፡፡

ዘንድሮ ትምህርትን ለማስቀጠል እና የባከነውንም ለማካካስ እንቅስቃሴ መደረጉን አስተውለን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶች ከችግሩ መውጣት ስላልቻሉ ሕጻናት እና ወጣቶች መጻዒ ሕይዎት እየተጎዳ ነው።

ወጣት ሴቶች ከትምህርት ገበታ ከራቁ እጣ ፈንታቸው ምን ሊኾን እንደሚችል ላሰበው የትምህርት ማቋረጥ አደጋውን መረዳት አያዳግትም። ‘እንኳን ዘንቦብሽ..’ እንዲሉ ድሮውንም በሴት ተማሪዎች ላይ ያለው ፈተና በርካታ ነው። ቤተሰብን ለማገዝ ከትምህርት መቅረት እና ያለ እድሜ ጋብቻ ደግሞ ተጠቃሽ ናቸው። ወጣት ሴት ከትምህርት ውጪ ስትኾን ያለ እድሜ ለመዳር፣ በሰው ቤት ሠራተኛ ለመኾን፣ ለስደት ወይም ለሌላ ችግር የመጋለጧ አደጋ የሰፋ ነው።

ወጣት ወንዶችም ቢኾኑ ጊዜያቸውን ለትምህርት በማዋል የነገን ተስፋ ሲሰንቁ እንጂ ከትምህርት ሲርቁ በነገ ላይ ተስፋ ይቆርጣሉ። ነገን በተስፋ የማያስብ ወጣት ደግሞ የራሱንም ኾነ የማኅበረሰቡን ሕይዎት እንደሚያናጋ መረዳት አያዳግትም።

ከትምህርት ገበታ ውጪ የኾኑ ከ4 ሚሊየን የሚበልጡ ተማሪዎች እንግዲህ የነገ ሕይዎታቸው ነው ዛሬ እየተበላሸ ያለው።

መምህራን ደኅንነታቸውን ጠብቀው ትምህርትን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ጥረት የሚገነዘባቸው አላገኙም።

ትምህርት ለዜጎች ብሎም ለሀገር ያለውን ፋይዳ ለተገነዘበ አይደለም በራስ ወገን ላይ በጠላትም ላይ የማይጨክኑበት የሕይዎት መንገድ ነው፡፡ ልጆችን ከትምህርት ማራቅ በትውልድ ላይ ጥፋትን መፍረድ ነው፡፡

ከቦታ ቦታ ቢለያይም ግጭት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተጠናከረ የመጣው የትምህርት ቤቶች መዘጋት ሁሉንም ዜጋ አሳሳቢ ነው፡፡ ስለኾነም ሕዝቡ የልጆቹ መጻዒ ሕይዎት እንዳይበላሽ ትምህርት እንዲቀጥል ጥረት ማድረግ አለበት።

ለግል ፍላጎት እና ጥቅማቸው ሲሉ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የሚፈልጉም እንዳሉ እናስተውላለን፡፡ ነገር ግን የነሱ የእንጀራ ገመድ የኾነው ተቋም ቢዘጋ ምን እንደሚሉ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ በሌሎች ላይ ሲኾን ቀላል የምናደርገውን ችግር በራሳችን ላይ ሲኾን ምን ያህል እንደምናከብደው ሳስበው የተስፋፋብንን ራስ ወዳድነት ያስገነዝበኛል፡፡

በራሳችን ሲደርስ እንደማንወደው ሁሉ ለፍተው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ምስኪን ወላጆች ሃሳብ እና ጭንቀት ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ለነገሩ ሕዝቡም ከአቅሙ በላይ ካልኾነበት በስተቀር የትምህርት ቤቶችን መዝጋት ወዶ የተቀበለው አለመኾኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

የልጆችን አለመማር በውይይት ካልፈታ “ተወው የኔን እግር እየበላ ነው” አለ እንደተባለው ነጋዴ እንኾናለን፡፡ የትምህርት ቤቶችን መዘጋት ጉዳት እንገነዘባለን፤ ግን ደግሞ ችግሩን ለማረም የምናደርገው ጥረት አነስተኛ ነው፡፡

የተማሪዎችን ሕይዎት የሚያበላሽ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ጨምሮ ማኅበራዊ ግልጋሎቶችን ማቋረጥ እና የምጣኔ ሃብት ተቋማትን ማውደም ከወዲሁ ካልተገቱ ነገ ከዚህም ለከፋ የእርስ በርስ ግጭት እና ለመጠፋፋት ላለመዳረጉ ዋስትና የለንም፡፡

‘በገጠር’ እና ‘አንዳንድ’ ብለን ያቀለልናቸው የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ወደ ሌሎች ተቋማት ላለመሸጋገሩ፤ በነጋ በጠባ የሚዘጋው መንገድ ከሰፈራችሁ አትንቀሳቀሱ ወደ ሚል ላለመጥበቡም ዋስትና የለንም፡፡

አቅም ያላቸው ጥቂቶች ልጆቻቸውን ወደ ሌላ ቦታ ልከው ለማስተማር ቢሞክሩም አብዛኛው አርሶ አደር እንኳንስ ወደ ሌላ ቦታ ሊልክ ቀርቶ በአካባቢው ትምህርት ቤቶችም ለማስተማር ችግሮች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ የቆዩ ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች ቢኖሩበትም ለመፍትሄያቸው በጋራ መሥራት እንጂ የትምህርት ቤቶችን መዘጋት በግዴለሽነት ማለፍ ውጤቱ ተመልሶ በተማሪዎችም በማኅበረሰቡም ትከሻ ላይ ማረፉ አይቀሬ ነው፡፡

እናም ማኅበረሰቡ በመመካከር የነገው ትውልድ ተረካቢ ሕጻናት ሕይዎት የሚገነቡ ትምህርት ቤቶችን መማር ማስተማር ሊያስቀጥላቸው ይገባል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሌማት ቱሩፋት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ መኾኑን አልሚዎች ገለጹ።
Next articleልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል