
ጎንደር: መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሰባት ወራት የሥራ አፈጻጸም ከዞን መንገድ መምሪያዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ እየገመገመ ነው።
በግምገማው ክልሉ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ የግንባታ ሥራዎች መሠራታቸው፣ ጥራት ያለው ዕቅድ በማቀድ ከፈጻሚ አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱ እና ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት የመምራት ተቋማዊ ባሕል ማሳደግ መቻሉ በጥንካሬ ተነስተዋል።
ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ የሥራ እንቅስቃሴ መገደቡ እና የጸጥታ ችግሩን ሰበብ በማድረግ አልፎ አልፎ ፈጻሚ አካላት ወደ ሥራ አለመግባት ደግሞ በውስንነት የተነሱ ናቸው።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ አስንቃ ክብካብ እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረግዚአብሔር ደሴ በክልሉ፣ በዞን በጀት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የመንገድ እና የድልይ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በጸጥታ እና በበጀት እጥረት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መስተጓጎል ሲገጥማቸው መቆየቱን የተናገሩት የሥራ ኀላፊዎቹ ጅምር ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በክልሉ 760 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የመንግድ ፕሮጄክቶቹ 2ሺህ 48 ኪሎ ሜትር ርዝመት አላቸው ያሉት ዶክተር ጋሻው በዚህ ዓመት 726 ፕሮጀክቶች ይጠናቀቃሉ ብለዋል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ብልጫ እንዳላቸውም አንስተዋል።
በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ከ63 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ከ32 በላይ የሚኾኑት ደግሞ ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት።
በጀት ዓመቱ 427 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾኑ ነው የገለጹት። 95 የድልድይ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። 42 የሚኾኑት ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደኾኑም አንስተዋል።
ቀሪ 53 የሚኾኑት የኮንክሪት ድልድይ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ክረምት ከመግባቱ በፊት እየተሠሩ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ይኾናሉ ነው ያሉት።
በመንገድ ጥገና በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት 17 ሺህ 624 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ታቅዶ እስካሁን ባለው ተግባር ከ9ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ተጠግነዋል ነው ያሉት።
የተጀመሩ የመንገድ እና ድልድይ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!