የጣና ሐይቅ ብዝኃ ሕይዎትን በቅንጅት በመጠበቅ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ገለጸ።

27

ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅ ብዝኃ ሕይዎትን በቅንጅት በመጠበቅ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ገልጿል።

ወይዘሮ እሰይነሽ አሳየ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወንዤጣ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ሳምንቱን ሙሉ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ከለማው የደንገል ተክል ላይ ጨፌ እየቆረጡ ይሸጡ እንደነበር ነግረውናል።

አሁን ላይ ግን የአካባቢው ማኀበረሰብ “የደንገል ተክሉ በመመንጠሩ የውኃው መሸሽ ለሕልውናችን አስግቶናል” በሚል ደንገል እንዳይቆረጥ መከልከሉን አንስተዋል።

እሳቸውም ሕጉን መጣስ በመፍራታቸው ከደንገል ላይ ጨፌ እየቆረጡ የመሸጥ የሠርክ ተግባራቸውን እንዳቋረጡ ነው የነገሩን።

ከጣና ሐይቅ ውስጥ ዓሳ አስግሮ በመሸጥ የሚተዳደረው ወጣት ደምሌ አማረ የደንገል ተክል ለበርካታ አእዋፍት እና ሌሎች በውኃ ላይ ለሚኖሩ እንስሳት መጠለያ በመኾን እንደሚያገለግል ነው የገለጸው።

የደንገል ተክል ባለበት የሐይቁ ክፍል ከፍተኛ የዓሣ ምርት እንደሚገኝ ተናግሯል።

በዘጌ ሰርጥ የልጆሜ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ካሳሁን ባይሌ ግለሰቦች የደንገል ተክልን ለታንኳ ፣ ለስፌት፣ ለቤት ጣሪያ እና ለአጥር መሥሪያ በሚል እንደሚመነጥሩት ተናግረዋል።

የተክሉን ሥርም በማንገል ውኃው ሲሸሽ ለሕገ ውጥ እርሻ እና ግጦሽ የሚጠቀሙ ግለሰቦች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በዚህም ምክንያት ተክሉ እየጠፋ በሄደባቸው የጣና ዳርቻዎችም ውኃው በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማኀበረሰብ የጣና ዳርቻዎችን ውኃ ገብ መሬት እንዳይታረስ፣ ደንገሉ እንዳይቆረጥ እና ቄጠማው እንዳይታጨድ በመከልከሉ አሁን አካባቢው መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ተወካይ ዳይሬክተር ጋሻው መሳፍንት 3ሺህ 156 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ያለው የጣና ሐይቅን ከሕልውና አደጋ ለመጠበቅ ማኀበረሰቡን እና ባለድርሻ አካላትን በማወያዬት መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተጨባጭ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።

ኤጄንሲው በሐይቁ የሚገኘውን ብዝኃ ሕይዎት የማልማት፣ የመጠበቅ፣ የመንከባከብ ኀላፊነቱን ለመውጣትም ከኀብረተሰቡ፣ ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ከሆቴሎች እና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ አዎንታዊ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል።

አሁን ላይ በባሕር ዳር ዙሪያ የጣና ሐይቅን ዳርቻዎች ከሕገ ወጥ እርሻ ተግባር መታደግ ተችሏል ነው ያሉት።

እየተመናመነ የነበረው የደንገል፣ የፊላ እና ሌሎች የብዝኃ ሕይዎት ሀብት ማገገም እንዲችሉ መደረጉንም ተናግረዋል።

የሐይቁን ዳርቻ ከየትኛውም የሕልውና ስጋት ለመጠበቅ እና ሐይቁን በዘላቂነት ለማልማትም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ልማቶችን ጎበኙ።
Next article” በዓመቱ 726 የመንገድ ፕሮጀክቶች ይጠናቀቃሉ” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ