
ጎንደር: መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ምክር ቤት 4ኛ፣ ዙር 12ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሔደ ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ምክር ቤቱ በ4ኛ ዙር 12 ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ያስቀመጠውን አቅጣጫ አፈፃፀም በተለያዩ ዘርፎች ሪፖርት አቅርበዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የውኃ ማፋሠሻ ቦይ፣ ድልድይ፣ የወጣቶች መዝናኛ እና ሌሎችም 56 ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልገሎት መሥጠታቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከ2016 በጀት ዓመት ተንከባለው የመጡ 13 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አቶ ቻላቸው ጠቅሰዋል።
ተንከባለው ከመጡ ፕሮክጀቶች አንዱ የቄራ ግንባታ ሲኾን ባጋጠመው ችግር ከክልሉ ገንዘብ ቢሮ እና ከከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ጋር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑ ተነስቷል።
ከሕገ ወጥ ግንባታ እና መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ እንዴትና በማን እንደሚፈፀም የመለየት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል። በሕገ ወጥ መንገድ በከተማዋ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አማካኝነት ተገንብተው የነበሩ 16 ቤቶች መፍረሳቸውን ጠቅሰዋል።
ችግሩ የዋለና ያደረ ቢኾንም በብስለት በመምራት ከክፍለ ከተሞች እና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በመኾን እየሠሩ መኾኑ ተነስቷል።
ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን