
ጎንደር: መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 12ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሔደ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እናትነሽ ዋለ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከባድ ቢሆንም በተደረገው ጥረት አንፃራዊ ሰላም መረጋገጡን ለምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል።
ለመጣው ሰላም ሕዝቡ፣ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት እንዲሁም የከተማው መሪዎች ለሠሩት ሥራ አፈ ጉባኤዋ አመስግነዋል። የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በቀጣይ ዘላቂ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባም አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።
አፈ ጉባኤዋ አክለውም ከቃል ወደ ተግባር በመሸጋገር የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥታት ዕድሳት እና የኮሪደር ልማቱ አበረታች ተግባር መኾኑን አንስተዋል።
የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም በቀጣይ መፈታት የሚገባቸው እና የሕዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መኖራቸውን አፈ ጉባኤዋ አስታውሰዋል።
በከተማዋ ያለእጅ መንሻ የመንግሥትን አገልግሎት ማግኘት ፈተና መኾኑ የጠቀሱት አፈ ጉባኤዋ የተደራጀ ሌብነት፣ በመዋቅሩ ሳይቀር የአስተሳሰብ ዝንፈት መኖር፣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ አሁንም የከተማዋ ችግር መኾኑን አንስተዋል። አፈጉባኤዋ ችግሮችን በመፍታት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን