
ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በስማዳ ወረዳ የሚገኘው የአጓት ውኃ የአፈር ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአርሶ አደሮች የመስኖ ልማት አገልግሎት እየሰጠ ነው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ውኃና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ በለጠ ተስፌን ጨምሮ የስማዳ ወረዳ እና የወገዳ ከተማ የሥራ ኀላፊዎች በግድቡ እየለሙ ያሉ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ግድቡን ተጠቅመው ስንዴ፣ በቆሎ፣ ድንች፣ ሽንኩርት እና ሌሎችንም በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዚህም አርሶ አደሮች ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የግብዓት አቅርቦት እና የገበያ ትስስር ችግሮች እንዲፈታላቸው በግድቡ እያለሙ ያሉ አርሶ አደሮች ጠይቀዋል።
የክንዶሜዳ ቀበሌ የመስኖ ባለሙያ ዳሳሽ አሻግሬ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የስማዳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በለጠ ጠቅል እንደገለጹት በአጓት ውኃ ግድብ 87 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ እና ከዚህ ውስጥ 28 ሄክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል።
በግድቡ 278 አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ያነሱት ኀላፊው ዘርፉ የብዙዎችን ሕይወት እየቀየረ ነው ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ውኃና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ በለጠ ተስፌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን የሠሩ እጆች የተባረኩ ይሁኑና አሁን ላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሲኾኑ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አቶ በለጠ ፕሮጀክቱ በርካታ ሀብት የፈሰሰበት በመኾኑ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በባለቤትነት መያዝ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በምልከታውም ሰላምን በማረጋገጥ እና ልማትን ማፋጠን ላይ መረባረብ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
መረጃው የስማዳ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን