ለመጭው መኸር 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገለጹ።

20

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለ2017/18 ምርት ዘመን ከተገዛው 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 2 ሚሊዮን ኩንታል ተጓጉዞ መድረሱን በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

በክልሉ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማረስ 186 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱንም ተናግረዋል።

ከግብዓት አቅርቦት አንጻር 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ገልጸው፤ እስካሁን 2 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ ተጓጉዟል ብለዋል።

በክልሉ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ለተጠቃሚው መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

ከመኸር ወቅት ምርት ማሳደጊያ ስልቶች ተደርጎ የተወሰደው የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እስከ መጋቢት 30 ሰፊ ንቅናቄ በማድረግ በሁሉም ዞኖች የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ሥራዎች 230 ሺህ ሄክታር በበጋ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ 200 ሺህ የሚሆነውን ወይም 90 በመቶ በላይ አፈጻጸም እንዳለው ተናግረዋል።

ሙሉ በሙሉ ያልተሳካበት ምክንያትም የመስኖ መሰረተ ልማት ከማሳካትና የውኃ ማሰባሰቢያ ከማሰራጨት አንጻር በነበሩ ክፍተቶች መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በቀጣዮቹ ጊዜያትም ግቡን ማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእስቴ – ስማዳ አስፋልት መንገድ ግንባታን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
Next articleነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች በመከናወን ላይ እንደማገኙ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ገለጸ።