” የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጸጋን ጥቅም ላይ ያዋሉ ናቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

103

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከተሞችን የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ.ር) በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በክልላችን ከተሞች ለሕዝባችን ቀልጣፋ አገልግሎትን መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

ከተሞችን ማዘመን፣ ለኑሮ ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፣ ገጽታን ማሻሻል እና ስማርት ሲቲ መፍጠር ወደ ሚያስችል ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያደርሱ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ የሚስተዋለውን ፈጣን የከተሞች መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ፣ የትራንስፖርት እና የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ለመፍታት ኮሪደር ልማት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ሰው ተኮር የኾነው ይህ ተግባር በምዕራፍ ተከፋፍሎ በጥራት እና በፍጥነት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ሁሉም የመሠረተ ልማት ባለድርሻ አካለትን በማስተሳሰር ከተሞችን ስማርት ሲቲ የማድረግ ሥራ የሁሉ አቀፍ ሥራ አካል መኾኑን ነው ያነሱት። “የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጸጋን ጥቅም ላይ ያዋሉ ናቸው “ብለዋል። የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች፣ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መብራት፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ይዟል ነው ያሉት።

የሕዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ ሥራ፣ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት፣ ነባር መስህቦችን ማደስ ለነዋሪዎች፣ ለኢንቨስተሮች እና ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ ሀገርን የሚገነቡ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ ከአልማ – ዋተር ፍሮንት ሆቴል ድረስ 40 ሜትር ስፋት ያለው ዘመናዊ መንገድ ሊሠራ ነው።