
ጎንደር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር መክሯል። በምክክሩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃኑ ጣምያለው፣ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናወጤ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ያሉበትን ሂደት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉጌታ ታደሰ ለውይይት መነሻ አቅርበዋል። የጎንደር ከተማን ገጽታ ለመቀየር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተዋል። ለሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የጎንደር ከተማ ሕዝብ ከፍተኛ እገዛ ማድርጉን ገልጸዋል።
የከተማዋን ውበት ለመጨመር እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል። በሁሉም ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የውይይት ተሳታፊዎች በከተማዋ የተሠሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የከተማዋን ገጽታ በተሻለ መንገድ እየቀየሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ሰላም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ውይይቶች በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች መደረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች አበረታች መኾናቸውንም አመላክተዋል። ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነት ማኅበረሰቡን እየፈተነው ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ለመፍትሔው መሥራት ይገባል ብለዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የተነሱ ሐሳቦች ለከተማዋ የሚጠቅሙ እና ተጨማሪ አቅም የሚኾኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የሰላም ሁኔታ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን የተናገሩት የቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ማኅበረሰቡም እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። ከአሁን በፊት በከተማዋ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት አንጻራዊ ሰላም መምጣቱንም ገልጸዋል። ለኑሮ ውድነቱ መባባስም የሰላም እጦቱ አንዱ መነሻ ምክንያት መኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝቡ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የከተማዋ ሰላም መጠበቁ ጎንደር ከተማ ተፈላጊ እንድትኾን አድርጓታል ነው ያሉት። ከተማዋን በማልማት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃኑ ጣምያለው የመንግሥት ሥርዓት መኖር እና መጠንከር ለልማት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል ። ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሰላምን ማምጣት ይገባልም ብለዋል። ሰላም በጎንደር እና አካባቢው ያለውን የመልማት አቅም በሚገባ ለመጠቀም እና የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ሚናው የጎላ መኾኑንም አስረድተዋል።
በጎንደር ከተማ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እና በጥራት ማከናወን መቻሉ የማኅበረሰቡን ትብብር እና እገዛ የሚያሳይ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:-ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን