
ከሚሴ: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጋራ የሰላም እና የልማት መድረክ ”ከረመዳን እስከ ረመዳን፤ ከትንሳኤ እስከ ትንሳኤ” በሚል መሪ መልዕክት በአጣዬ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ከአጣዬ እና ከሰንበቴ ከተሞች እንዲኹም ከኤፍራታና ግድም ወረዳ እንዲኹም ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮችን ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች እና የሀገር መከላከያ መኮንኖች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የአጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ቀጣናው በጸረ ሰላም ኃይሎች ሲደፈርስ እንደነበር ገልጸው አኹን ላይ በተሠራው ሥራ ወደ ሰላም ተሸጋግሯል ብለዋል። ከነበሩበት ቁርሾ በመውጣት በጋራ መገበያየት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
የአጣዬ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተመስገን አሰፋ ባለፈው ዓመት ረመዳን ላይ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በጋራ በተሠራው ተግባር አጣዬ ከተማ እና አካባቢው ሰላሙ ተረጋግጦ ወደ ልማት ተሸጋግረናል ብለዋል።
አሁን ላይ ከግጭት በመውጣት በጋራ ወጣቶች ስፖርታዊ ውድድር የሚያዘጋጁበት እና በጋራ የሚገበያዩበት ኹኔታን መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ የተሠራው ሕዝብን ያሳተፈ ተግባር ውጤት በማምጣቱ ቀጣናው ወደ ልማት ሥራዎች ተሸጋግሯል ነው ያሉት።
በቀጣናው ግጭት ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላትን ለማምከን ሁለቱ አጎራባች ዞኖች በቅንጅት እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በቀጣናው ጠንካራ ሰላም በመገንባት የልማት አካባቢ እንዲኾን እየሠራን ነው ብለዋል።
በቀጣይ ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች ያደሩ መሬቶችን በማረስ ወደ ምርት ለማምጣት ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት። የጥፋት ቡድኖችም ከድርጊታቸው በመቆጠብ የሰላም አማራጭን ሊከተሉ እንደሚገባም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!