
ደብረማርቆስ: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን እየተገነቡ ያሉ የመሥኖ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ ገምግሟል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአርሶ አደሮችን ሕይዎት የሚለውጡ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው የመሥኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን መሥኖ እና ቆላማ አካባቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጥላሁን ንጋቱ ከ11 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ፕሮጄክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል። ፕሮጄክቶሹ ከ6ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እንደሚያለሙ ገልጸዋል።
የመሥኖ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው በመዘግየቱ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻሉም ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለመሥኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቅ ተባባሪ ሊኾኑ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የዞኑን በመሥኖ የመልማት አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ፕሮጄክቶቹ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እና የአርሶ አደሮችን ሕይዎት በዘላቂነት እንዲለውጡ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ፕሮጄክቶቹ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እገዛ ያላቸው በመኾኑ የወረዳ መሪዎች እና ሙያተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የመሥኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሚጠቅሙ መኾናቸውን ገልጸዋል። ፕሮጄክቶቹ በጥራት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ርብርብ እና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። የመሥኖ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ውል የያዙ አካላትም የጸጥታ ችግርን ሳያሳብቡ የያዙትን ፕሮጀክት ሊፈጽሙ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የወረዳ አሥተዳደር ተቋማት መሪዎች እና ሙያተኞችም ግንባታዎችን በየጊዜው በመከታተል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ለመሥኖ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት እና ረጅ ድርጅቶች ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙም ተገልጿል። በዞኑ ከ43 በላይ ነባር የመሥኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እየተከናወነ መኾኑን ተመላክቷል። የ13 የመስኖ ፕሮጀክቶች ሥራ መቆሙም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!