ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ።

19

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ለጊዮን ሁለተኛ ደረጃ፣ ለአጼ ሠርጸ ድንግል መላክ ሰገድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ለፊታውራሪ ሃብተማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 30 ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተር፣ ስድስት ራውተር እና የስድስት ወር የኢንተርኔት ፓኬጅ ድጋፍ አድርጓል።

የፊታውራሪ ሃብተማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ህሊና ታደለ ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ በትምህርታችን ከጊዜው ጋር እንድንሄድ ያደርገናል ብላለች። የብዙ ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ችግር እንደነበር እና ድጋፉ ችግሩን ለመቀነስ እንደሚረዳም ገልጻለች።

የአጼ ሠርጸ ድንግል መላክ ሰገድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ዓባይነህ የሽዋስ ለትምህርት ቤታቸው የተደረገው የአስር ላፕቶፕ ድጋፍ ለዲጂታል ቤተ መጻሕፍት እንደሚጠቅም ገልጸዋል። ተማሪዎቻችንም ቴክኖሎጂን እንዲያውቁ ያደርግልናል ነው ያሉት።

በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሰሜን ምሥራቅ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጥላሁን ብርሃኑ በአብሮነት ወደፊት በሚል መሪ መልዕክት የተደረገው ድጋፍ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው ገልጸዋል። በአብሮነት ወደፊትን ስንተገብር ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታላይዜሽን በመጠቀም ተማሪዎችን ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 100 ወገኖች የጤና መድኅን ሽፋን የሚኾን የ150 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል። የሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከተቋማት እና ከማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ሳፋሪኮም ለነገው ትውልድ በማሰብ እና በቴክኖሎጂ ከዓለም ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። ትውልድ ተወዳዳሪ መኾን የሚችለው ትምህርት ቤቶች ላይ በሚሠራው ሥራ ነው ያሉት ኀላፊው ትምህርትን በቴክኖሎጂ መደገፍ ወሳኝ መኾኑ ገልጸዋል።

የተደረገውን ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግሰው መለሰ ሳፋሪኮም ትምህርት ቤቶችን ከዘመኑ ጋር ለማስተሳሰር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፉ ትምህርት ቤቶችን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን እና ትውልዱን የሚደግፍ መኾኑን ገልጸዋል።

ዓለም በቴክኖሎጂ እየተሻሻለ በመኾኑ የዚህ ተሳታፊ ትውልድ ለመፍጠር ቴክኖሎጂን መጠቀም ትክክለኛ ምርጫ እና ግዴታ መኾኑንም ገልጸዋል። ሌሎቹም እንድደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። በኮምፒዩተር እና ራውተር ርክክቡ ወቅት ለጤና መድኅን አገልግሎት ድጋፍ የሚውለው የ150 ሺህ ብር ቼክም ርክክብ ተደርጓል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኅብረት ሥራ ማኅበራትን አገልግሎት የሚያሻሽል ሥራ እየሠራ መኾኑን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ገለጸ።
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰጣቸው ዕውቅና ምስጋና አቅረቡ።