
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ52 ሚሊዮን ብር የቅርስ ጥገና ሥራ እየተሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ገልጿል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቤል መብት ዞኑ በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች መገኛ ነው ብለዋል። እነዚህ ቅርሶች በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ምክንያቶች ለጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ለጉዳት የተጋለጡ ቅርሶችን ተጨማሪ ምጣኔ ሃብት እንዲያመነጩ በመንግሥት በጀት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የሰባት ቅርሶች የጥገና ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ የጉዛራ ቤተ መንግሥት ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በጀት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ሌሎቹ ቅርሶች በክልሉ መንግሥት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እየተሠሩ የሚገኙ ናቸው።
ጥገና እየተደረገላቸው የሚገኙ ቅርሶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
