
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ፓርቲው ባለፉት ጊዜያት የሠራቸውን ሥራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ፓርቲው ሀገራዊ ሰላምን ለማምጣት የተከተለዉ በመርህ ላይ የተመሠረተ አካሄድ የጸረ ሰላም ቡድኖችን ዓላማ እና ሕልዉና ያከሸፈ መኾኑን አንስተዋል።
የለውጡ መሪ ከመነሻዉ ጀምሮ እየተከተላቸዉ የሚገኙት ሀገራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረጉ፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት እና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ልማትን እውን የማድረግ መርሆዎች መኾናቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ሁሉም ማዕዘናት ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ያለው ቁርጠኛ አቋም ፍሬዎችን ማሳየት መጀመራቸውንም አንስተዋል። የፓርቲውን እሳቤዎች እና ሀገራዊ ራዕይ ትክክለኛነትን ማረጋገጥ የቻለ መኾኑን ገልጸዋል።
የፓርቲው ጥረቶች በአማራ ክልል ከፍተኛ ስኬቶችን ያስመዘገበ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የክልሉን ሰላም እና የሕዝቡን ደኅንነት ለአደጋ አጋልጠው የቆዩትን ጸረ ሰላም ቡድኖች እውነተኛ ማንነት እና ዓላማ ሕዝብ አንዲገነዘበው ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል። ጸረ ሰላም ኀይሎች በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ መዳከማቸውንም ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከምሥረታው ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን እውን የማድረግን ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳው ነው ብለዋል። ፓርቲው የማኅበረሰብ ውይይትን በስፋት በማካሄድ፣ ከታሪክ የተወረሱ ሀገራዊ የትርክት ቅራኔዎችን ለመፍታት በመሥራት እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማምጣት የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራቱንም ገልጸዋል። ሁሉን አቀፍ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላምን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሢሠራ መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊው የአማራ ክልልን ለማተራመስ ሲጥሩ በነበሩ ጸረ ሰላም ቡድኖች በርካታ ፈተናዎችን ሲያስተናግድ መቆየቱን አስታውሰዋል። በፓርቲው እና በሕዝቡ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ምክንያት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ክልሉ ለውጦችን እውን ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረትም የጸረ ሰላም ቡድኖች ተጽዕኖ በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል። በአንድ ወቅት በአመጽ እና አለመረጋጋት ሲታመስ የነበረው የአካባቢው ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት የተሻለ የሰለም እና መረጋጋት ሁኔታ ላይ አንደሚገኝም ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ችግሩን ለመፍታት መሠረታዊ የማኅበረሰብ ተሳትፎን በማበረታታቱ፣ በሕዝብ ባለቤትነት በሚመራ ስልት ላይ ትኩረት በማድረጉ፣ የጽንፈኛ ቡድኖችን አጀንዳዎች እና ዓላማዎች በማክሸፍ ዜጎች በጋራ ኾነዉ በሰላም ዙሪያ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ጠቅሰዋል።
“የተሻሻለው የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ ልማትን እያበረታታ ነው” ብለዋል። የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የግብርናን ማዘመን ውጥኖች እና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ማስፋፊያ መርሐ ግብሮች ያለ ምንም እንቅፋት እየተተገበሩ እና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በአማራ ክልል ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የተመዘገቡት ድሎችም በብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ እና በመርህ ላይ የተመሠረተ አመራር መኾኑን ነው ያሰኑት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!