ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው።

11

ደሴ: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። በቅርበት ከሚገኘው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ዝግጁ የማድረግ ተግባር መከናወኑን የመምሪያው ኀላፊ መንግሥቱ አበበ ተናግረዋል።

ያነጋገርናቸው የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመምህራን እና ወላጆች ድጋፍ ለተሻለ ውጤት እንበቃለን ብለዋል። ጊዚያቸውን በቤተ መጻሕፍት ቤት እንደሚያሳልፉ የተናገሩት ተማሪዎቹ እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕላቸውንም እያሳደጉ መኾናቸውን ገልጸውልናል።

መምህራንም የእረፍትጊዜያቸውን ጭምር ለተማሪዎች እየሰጡ እንደኾነ ተናግረዋል። ተማሪዎችን በደረጃ በመለየት እየተማሩ ነው፤ ልዩ ድጋፍ በማድረግም ተማሪዎች ለተሻለ ውጤት ለማብቃት እየተጋን ነው ብለዋል። ወላጆችም ልጆቻቸውን በመከታተል ቁጥጥር እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። ስለመማር ማስተማር ሂደቱ በተመለከተም በመወያየት ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ የወደሙ እና የተዘረፉ ቢኾኑም ከማኅበረሰቡ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመኾን የትምህርት ቤቶችን ግብዓት የማሟላት ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መኾኑን ለአሚኮ ገልጸዋል ።

ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናን ለሚወስዱ ተማሪዎች ከወሎ ዩኒቨርስቲ ጋር በመነጋገር የሥነ ልቦና ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል። “ጊዜው የቴክኖሎጂ በመኾኑ ተማሪዎቻችንም በዚህ ሂደት ማለፍ አለባቸው” ያሉት መምሪያ ኀላፊው ትምህርት ቢሮም ኾነ ትምህርት ሚኒስቴር ለቤተ ሙከራ እና አይሲቲ ዘርፎች ልዩ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ 41ሺህ 132 ተማሪዎች በመማር ላይ መኾናቸውን ተገልጿል።

ዘጋቢ: ኃይሉ መላክ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
📸 ተመስገን ስሜነህ

Previous articleርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር ተወያዩ።
Next articleየስኳር በሽታ እና አሳሳቢነቱ!