
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና ሌሎችም የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ እና ሌሎችም የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ እንደ ሀገር በሚደረገው የምክክር ሂደት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ሁሉንም ያካተተ እና ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው። ከውይይቱ በኋላ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ምክክር እና ውይይት ከየትኛውም አይነት ደም አፋሳሽ ጦርነት ጀምሮ መጠነኛ አለመግባባቶችንም በመፍታት ሰላም ለመገንባት የሚያገለግል መሳሪያ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
እንኳንስ በምክክር እና ውይይት የዳበረ ልምድ ያላት ኢትዮጵያ ሌሎችም በርካታ የዓለም ሀገራት በመመካከር እና በመወያየት የግጭት ምዕራፋቸውን ዘግተዋል፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም የማያስማሙንን ጉዳዮች በሙሉ ወደ ምክክር በማምጣት መግባባት እና ዘላቂ ሰላም መገንባት ይገባናል ነው ያሉት።
ዶክተር ዮናስ ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን በተሳካ ኹኔታ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በአማራ ክልል አካባቢዎችን ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ብሎ በመመደብ የአጀንዳ መነሻ ሐሳቦችን የማሠባሠብ ሥራ በስኬት መከናወኑን ገልጸዋል። በክልል ደረጃ የሚሳተፉ ወኪሎችንም መምረጥ ተችሏል ብለዋል።
የአማራ ክልል መሪዎች እና ሕዝቡ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደኾነም ገልጸዋል። አኹን ላይ እንደሀገር በሚደረገው ዋናው ምክክር የሚቀርቡ የአማራ ክልል አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ላይ ነን ብለዋል። በዋናው እና የመጨረሻው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የአማራን ክልል ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችም እየተመረጡ መኾኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ማንኛውም አይነት ጥያቄዎች ለውይይት ቀርበው እልባት የሚያገኙበት ነው፤ እንደ አማራ ክልልም ሕዝቡ ንቁ ተሳታፊ በመኾን ለዘመናት የሚያነሳቸውን አጀንዳዎቹን ወደ ምክክሩ ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ነጻ እና ድልድይ ኾኖ በመቆም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምክክር ጠንካራ ባሕል ኾኖ እንዲቀጥልም እየሠራን ነው ብለዋል።
ዛሬ ከአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በተደረገው ውይይትም ክልል አቀፍ ምክክሩ በስኬት ለማከናወን በሚያስችሉ ሂደቶች ላይ ተነጋግረናል ብለዋል። ዶክተር ዮናስ ግጭቶች ባሉባቸው ሌሎች ክልሎች ውስጥ ውጤታማ ክልላዊ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል። በኦሮሚያ አካባቢዎች ምክክሩ ውጤታማ እንዲኾን ያስቻለው ሕዝቡ ለሀገራዊ አጀንዳዎቹ የሰጠው ትኩረት እና ብርታት እንዲኹም በየአካባቢዎች የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክር ያላቸው ቁርጠኝነት ስለመኾኑም አብራርተዋል።
አማራ ክልልም በግጭት ውስጥ የቆየ መኾኑ ይታወቃል፤ ግጭት አማራ ክልል ብቻ ሳይኾን በሌሎችም ክልሎች አለ፤ ይህንን ለማስቆም እና የተሻለውን ሰላም ለመትከል ሁሉም ለምክክር ልቡን መክፈት አለበት ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። ሕዝቡ የግጭት ምክንያቶችን ከመሰረቱ መለየት እና በሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ይዞ መቅረብ አለበት፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኘውም ይሄው ነው ብለዋል ዶክተር ዮናስ።
“በግጭት ሰበብ የሰው ደም ከመፍሰሱ እና ንብረት ከመውደሙ በተጨማሪ ከ4 ሚሊዮን በላይ የአማራ ክልል ተማሪዎችን ከትምህርት ጉዟቸው ሲሰናከሉ አይተናል፤ ይህ ሁሉ ተማሪ ከእውቀት ተገልሎስ ምን አይነት ክልል እና ሀገር መገንባት ይቻላል? ከዚህ በላይ የግጭትን አስከፊነት በጉልህ እንደሚያሳይ አስከፊ ነገርስ ከወዴት ይምጣ?” ሲሉም አጠይቀዋል። ሰላምን በሰላማዊ መንገድ መገንባትን ባሕል ማድረግ አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከግጭት ወጥታ ጠንካራ የምክክር እና የውይይት ባሕል ያላት ሀገር እንድትኾን ሁሉም የበኩሉን ማድረግ አለበት ነው ያሉት። እንደ አማራ ክልል በሚካሄደው የምክክር ሂደት ውስጥ መላው ሕዝብ ንቁ ተሳታፊ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል። በግጭት ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችም ቢኾኑ ከየትም የመጡ ሳይኾን የኛው ቤተሰቦች ናቸው፤ ይህንን ግጭት በንግግር መፍታት እንደሚቻል ጽኑ እምነት አለን፤ ከግጭት ሊያወጣ የሚችል ጥያቄዎቻቸውን እና አጀንዳቸውን በተወካዮቻቸውም ይኹን በሚመቻቸው መንገድ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቢያቀርቡ ለመቀበል ዝግጁ ነን ብለዋል።
ዶክተር ዮናስ አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመስጠት በርካታ አማራጮች እንዳሉም ጠቁመዋል። በግለሰብ ደረጃ፣ በተለያዩ ማኅበራትና አደረጃጀቶች፣ በተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እና በሌሎችም ማንኛውም መንገድ አጀንዳን መስጠት ይገባል ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ ሰላም ሲባል ማንኛውም እድሜው የደረሰ ሁሉ የምክክር ሂደቱን በሚችለው መንገድ ሁሉ ይደግፍ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ሚዲያዎችም የኮሚሽኑን ቁርጠኛ የሰላም አቋም በማሳወቅ እና ሕዝብን ለሰላም በመቀስቀስ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
