
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከዞን፣ ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከብሔራዊ ፓርኮች እና ከማኀበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት የዘርፉ መሪዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እንዲኹም የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለተከተ በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል።
የክልሉ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ ዛሬ ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠበቅ ካልቻልን ነገ ለውጤት መብቃት አንችልም ብለዋል። እንደ ጣና ሐይቅ እና ዓባይ ወንዝ ያሉትን በርካታ የውኃ ሀብቶች በመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለማግኘትም በትጋት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ክልሉ በጸጥታ ችግር በመቆየቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ጥብቅ ሥፍራዎች በልዩ ትኩረት በአግባቡ በመጠበቅ እንዲያገግሙ የማድረግ ተግባር እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ የማሳደግ ኀላፊነት አለብን ያሉት አቶ ተስፋሁን ብዙኃ ሕይዎቱን ከጉዳት ለመታደግ በትብብር እየሠራን እንገኛለን ብለዋል። የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ በክልሉ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ደን በመከለል እንዲጠበቅ እየተደረገ እንደኾነም አንስተዋል።
ደንን መጠበቅ ብቻ ሳይኾን ለገቢ ምንጭነት እንዲውል እየተደረገ ነው ያሉት አቶ በልስቲ ለዚህ ተግባር የሚውሉትን የደን ዓይነቶች መለየት እና ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የአማራ ክልል ከደን ውጤቶች እና ግብይት በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ብር እንዲያገኝ የሚያስችሉ ተግባራት መከናዎናቸውንም ተናግረዋል። ከውጭ ሀገር የሚገባን የደን ውጤትም በሀገር ውስጥ እንድመረት ማድረግ እየተቻለ ነው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ዘርፍ 55 ሺህ በላይ ወገኖች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት። በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች ከ10 በላይ የማኀበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮችን በመጠበቅ ለትውልዱ ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው ተብሏል።
የአረንጓዴ አሻራ እና የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭን ለማስቀጠል ባለፉት ወራት በርካታ የማኀበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ400 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክ ተሰብስቦ እንድወገድ ተደርጓል ነው ያሉት። 315 ሺህ በላይ ሜትሪክ ኪዮብ በላይ ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብ ተችሏልም ብለዋል።
የአቡነ ዮሴፍ እና አቡሃይ ጋሪያ ጥብቅ የማኀበረሰብ ሥፍራ ኀላፊ ዲያቆን አወቀ መለሰ በ18 ቀበሌዎች ከ16 ሺህ በላይ የኀብረተሰብ ክፍልን በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች በመከፋፈል ጥብቅ ሥፍራዎችን እንዲንከባከብ እና እንዲጠቀም የማድረግ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
በአካባቢው የሚገኘው የጓሳ ሳር በአግባቡ በመጠበቁ በዚህ ዓመት ከ80 ሚሊዮን በላይ ብር መገመቱን ተናግረዋል። በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋጡማ መሐመድ በአካባቢው የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብቶች የመንከባከብ ሥራ አከናውነናል ብለዋል።
በቀጣይም ያለውን ውስንነት በማረም ዕቅድን መቶ በመቶ ለመፈጸም ተግባብተናል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ