
ከሚሴ: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች የጋራ የሰላም እና የልማት መድረክ በጨፋሮቢት ከተማ ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ ከአርጡማ ፉርሲ ወረዳ፣ ከአንፆኪያ ገምዛ እና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የአጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች ሁለቱ አጎራባች ነዋሪዎች የተዛመዱ እና ሊነጣጠሉ የማይችሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ይህን የተጋመደ ማኅበረሰብ ለመነጣጠል የሚሠሩ አካላትን ለመጨረሻ ጊዜ በቃችሁ በማለት ከመንግሥት ጋር ኾነን ልንታገላቸው ይገባልም ብለዋል። የማኅበረሰብ የእርስ በእርስ ግንኙነት እና የአንድነት ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ እንሠራለንም ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ ዓሊ ቀጣናውን የግጭት ሳይኾን በጋራ እያለሙ በጋራ ምርት የሚያቀርቡበት ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ሕዝብን ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በተሠራው ተከታታይ የሰላም ግንባታ ሥራ ቀጣናውን ላለፈው አንድ ዓመት ወደ ሰላም ማሸጋገር መቻሉን ገልጸዋል። የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲኾንም እስከ ቀበሌ ድረስ በሁሉም አዋሳኝ አካባቢዎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር በትብብር ይሠራልም ብለዋል። ሕዝብን ለመነጣጠል በሚሠሩ አካላት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን