
አዲስ አበባ: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በትግራይ ክልል ሕገ ወጡ ቡድን የመፈንቅለ መንግሥት ተግባር መፈጸሙንም አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል አኹን ያለው ወቅታዊ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሕግ ተቀባይነት ያጣ ቡድን ለግል ጥቅሙ የፈጠረው ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማደናቀፍ እና ክልሉን ወደ ግጭት ለመመለስ ኾን ተብሎ የተደረገ ነውም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም በፌዴራል መንግሥቱ ተሳትፎ እና ይሁንታ የተመሰረተው ጊዜያዊ አሥተዳደሩ አደጋ ላይ ሲወድቅ እና ሕዝቡ ለዳግም ጦርነት ሲዳረግ መንግሥት የመከላከል ኀላፊነት እና ግዴታ እንዳለበትም ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተኩስ ማቆም እና እንደሀገር አንድ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ዋና ዓላማው ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ሙሉ በሙሉ የታጠቁ ኀይሎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስም የስምምነቱ ዋና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሥልጣን ፍላጎት ያላቸው ኀይሎች ተፈፃሚነቱን ለማስተጓጎል በግልፅ እየተንቀሳቀሱ እና የጊዜያዊ አሥተዳድሩን ሥልጣን ለመንጠቅ በመሳሪያ ጭምር ታግዘው እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሰላም እና ልማት ይገባዋል ያሉት አቶ ጌታቸው ሕገ ወጥ ያሏቸውን ቡድኖች ቢሮዎችን በመስበር፣ ማህተሞችን በመዝረፍ፣ በግልፅ የፍንቀላ ተግባር እየፈጸሙ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለውም ከዚህ ቀደም ክልሉ ውስጥ ላሉ ችግሮች ምክንያቶችን ውጫዊ በማድረግ የፌዴራል መንግሥቱን ስንወቅስ የነበረ ቢኾንም እውነታው ግን ክልሉ ለገባበት ምስቅልቅል ተጠያቂዎቹ እኛው ነን ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮችን በተመለከተም ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በተለያየ መንገድ እክል የተፈጠረው በእኛው ችግር ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ይህም የኾነው የፖለቲካ ትርፍ ስላለው ነው ብለዋል፡፡
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረትም ትጥቅ የማስፈታት እና ታጣቂዎችን ወደ ተሐድሶ ማስገባት የነበረብን ቢኾንም በራሳችን ችግር ምክንያት ተፈጻሚ አለመኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን