
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ እና ልዑካቸውን ተቀብለው አነጋግረዋል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው። የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ዋነኛ አላማ የኢትዮጵያ እና የኩባን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 50ኛ አመት ለማክበር፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ታሪካዊ ወዳጅነትና ትብብር በጉልህ ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል።
ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ የፓርቲና የመንግሥት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ የኢትዮጵያና ኩባ ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት መኾኑን ገልጸዋል። ኩባ በየዘመናቱ ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍና የማይናወጥ አቋም አድንቀዋል፡፡
ኩባውያን ባለሙያዎች በተለይ በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ዘርፎች ከፍተኛ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት። የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ፣ የቢሾፍቱ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅን በማቋቋም ሂደቶች ላደረጉት እገዛ እና ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለተሰጡት የትምህርት እድል እውቅና ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶችም ገልጸውላቸዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መረጋጋትን በማስፈን ያላትን ሚና፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ የሽግግር ፍትሕንና ሀገራዊ ምክክርን ለመተግበር እያደረገች ያለችውን ጥረትም አንስተዋል። ” ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር በዋና ዋና ዘርፎች ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት” ብለዋል። ብልጽግና ፓርቲም ለግንኙነቱ መጠናከር ያለውን ድርሻ ከፍተኛ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ኩባ የረዥም ጊዜ ወዳጅት ለመሰረተችባቸው ሀገራትና አጋሮቿ ታማኝ አጋር መኾኗን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ አጋርነት ከዚህም በላይ ለመማሳደግ ቁርጠኛ መኾኗን ተናግረዋል። በኩባ ላይ ለረዥም ዓመታት ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ አንዲነሳ በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ ሲያቀርብ ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ከሁለቱም ሀገራት የጋራ ራዕዮችና ግቦችም ሁሉን አቀፍ ሰላምና ደኅንነት እውን ማድረግ አንደኛው መኾኑን አንስተዋል። በሁለት ቀን ቆይታቸው የኢትዮጵያ መንግሥትና የብልጽግና ፓርቲ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ አመስግነዋል። ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነትና ትብብር ከፍ ለማድረግ ያላትን ጽኑ አቋም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!