የጤና ባለሙያዎች የጸጥታ ችግር ሳይበግራቸው ማኅበረሰቡ ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ ማድረጋቸውን አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ ገለጹ።

10

ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን አክብሯል። በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት ላስመዘገቡ ሴቶች እውቅና ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ሲከበር ቀኑን ከማሰብ ባለፈ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት የሚደረግበት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲም የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ተደራሽነት በማስፋት ቤት ለቤት፣ በማኅበረሰብ እና በጤና ኬላ ደረጃ አገልግሎቱ እንዲሠጥ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል። የጤና ባለሙያዎች ክልሉን ያጋጠመው ጦርነት ሳይበግራቸው ማኅበረሰቡ ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና በመስጠት ሕይወት እንዳይጠፋ አድርገዋል ነው ያሉት። ይህም በተላላፊ በሽታዎች ይሞቱ የነበረውን የሕጻናት እና የእናቶችን ሞት በመቀነስ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት ችለዋል ብለዋል።

አሁን ላይም በሁሉም መስክ የሚገኙ ሴት የጤና ባለሙያዎች ወቅታዊ ችግር ሳይበግራቸው የጤና አገልግሎቱን በጥራት፣ በፍትሐዊነት እና በዘላቂነት ማኅበረሰቡን እያገለገሉ መኾኑን ነው የገለጹት። ሴቶች በሆስፒታሎች፣ በዞን መምሪያዎች እና በቢሮ ደረጃ በኃላፊነት ማኅበረሰቡን እያገለግሉ እንደሚገኙም አንስተዋል።

በክልሉ ዘላቂ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት የጤና የሥራ ኀላፊዎችን አቅም ለማሳደግ ሥልጠና እየተሠጠ መኾኑን ገልጸዋል። ሥልጠናው ለሴቶች ትኩረት የሰጠ ነው ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleእውቀትን የተከለከሉ የሀገር ተረካቢዎች!
Next articleየአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት አሠራሩን ለማዘመን የሚያስችል የልምድ ልውውጥ አደረገ።