እውቀትን የተከለከሉ የሀገር ተረካቢዎች!

19

ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙዎች ትምህርትን ፍለጋ ተራራ ወጥተዋል፤ ቆልቁለት ወርደዋል፡፡ በባዶ እግራቸው እየተጓዙ በእሾህ ተወግተዋል፡፡ በጋሬጣ ተሰቃይተዋል፡፡ በፀሐይ ሐሩር፣ በዝናብ ቆፈን ተመላልሰዋል፡፡ ብልሆች ዕውቀትን በመብራት ፈልገዋታል፡፡ የት ነሽ እያሉ አስሰዋታል፡፡ ዋሻ ለዋሻ ተከትለዋታል፡፡ በአገኟትም ጊዜ አብዝተው ተደስተውባታል።

ከአበው እግር ስር ተቀምጠው ጠብቀዋታል፡፡ አበው በነገሯቸው ጊዜም በትሕትና ተቀብለዋታል። በብልሃት ይዘዋታል። ዝቅ ብለው ተቀብለው ከፍ ብለው ኖረውባታል። በመብራት በፈለጓት ዕውቀታቸው ሀገር ሠርተዋል፡፡ ትውልድ አንጸዋል፡፡ በየዋሻው በየሐይቁ የዕውቀት ማዕድ አዘጋጅተዋል፡፡ ትውልድን ሁሉ የሚያጠግብ የዕውቀት መሶብ ዘርግተዋል፡፡ እኒያ ጠቢባን ለዕውቀት ታላቅ ክብር ሰጥተዋል፡፡ ባከበሯት ልክም በዕውቀት ተጠቅመዋል፡፡ ሀገር ያጸኑት፣ አንድነትን በአለት ላይ ያጸኑት፣ ነጻነትን ደመቅ አድርገው የጻፉት በጥበብ ነው።

በሐይቅ ላይ ገዳም የገደሙት፣ በዓለት ላይ አብያተ መቅደስ ያነጹት፣ ጨርሰው የጀመሩት፣ ከጣሪያ ወደ መሠረት የወረዱት፣ አቤት እንደ ምን ያለ ሥራ ነው እያስባሉ ዓለሙን ሁሉ ያስደነቁት፣ ጡብ ደርድረው እጹብ የተባሉ አብያተ መንግሥታትን ያሳመሩት፣ ፊደል ቀርጸው፣ ብራና ፍቀው፣ በአፍ ያለ ይረሳል፣ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል እያሉ ቀደም ሲል በአለት ላይ፣ በኋላም በብራና ላይ ታሪክን ያሰፈሩት ለዕውቀት ክብር ስለነበራቸው ነበር፡፡

ያከበሯት ዕውቀትም አስከበረቻቸው፡፡ ያከበሯት ጥበብም በትውልድ ሁሉ ግርማና ሞገስን አስችራቸዋለች። እነኾ ዛሬ ግን ጠቢባን በመብራት የፈለጓት፣ ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ሰንጥቀው የተጓዙባት፣ ትምህርት በአፈሙዝ ትዘጋለች። በሰይፍ እና በሰልፍ ትከለከላለች። የዕውቀት በሮች ይቆልፋሉ።ዕውቀትን የተራቡ ልጆች ጾም ውለው ጾም ያድራሉ። ዕውቀትን የሚሰጡ መምህራን ይሳደዳሉ። ይገፋሉ።

እነኾ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። በድቅድቅ ጨለማ ኩራዝ እያበሩ ነገን ብርሃን ለማድረግ ለትምህርት የሚተጉት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከተከለከሉ ጊዜያት አልፈዋል። በኩራዝ መብራት ዕውቀትን እያሰሱ፣ ለእግሮቻቸው ጫማ እንኳን ሳይኖራቸው ያስተማሯቸው ወላጆቻቸው ያልፍላቸው ዘንድ የሚታትሩት ተማሪዎች ከትምህርት ተከልክለው በቤት ውስጥ ውለዋል።

ከዛሬ ነገ የዕውቀት ቤታችን ትከፈታለች፣ ከዕውቀት አባቶቻችን ጋር የምንገናኝባት ጊዜ ትመጣለች ብለው ተስፋን ያደረጉ ተማሪዎች ተስፋቸው እየራቀች፣ ዘመናቸውም በከንቱ እየባከነች ጊዜያት አልፈዋል። ዛሬም ጊዜያቸው በከንቱ እያለፈች፣ ዕድሜያቸውም እየባከነች ነው። በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል። ትምህርት ቤቶች በአፈሙዝ ከተዘጉ ከዓመት ከመንፈቅ በላይ ተሻግረዋል። መምህራን እና ተማሪዎች ተነፋፍቀዋል። ልጆቻቸውን ከጓደኞቻቸው እኩል ለማድረግ እነርሱ ሳይጎርሱ ያጎረሱ፣ እነርሱ ሳይለብሱ ያለበሱ ወላጆች በሀዘን ተቀምጠዋል። በአፈሙዝ የተዘጉት ትምህርት ቤቶች መቼ ይከፈቱ ይኾን? ተጽዕኖውስ ስንት ትውልድ ይሻገር ይኾን?

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አማካሪ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ትውልድ በዕድሜው ደረጃ እና ሂደት በዕውቀት እየታነጸ ሲሄድ ሀገርም አብራ ትታነጻለች፡፡ ያ ሳይኾን ሲቀር ግን ትውልድም ይጎዳል ሀገርም ትጎዳለች ይላሉ። ልጆች በልጅነታቸው ትምህርትን መቀበል በሚገባቸው ጊዜ መቀበል አለባቸው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በተለያየ ምክንያት ትምህርት ይቋረጣል፡፡ ልጆች በዕድሜያቸው ልክ ማግኘት የሚገባቸውን ሳያገኙ ይቀራል፡፡ ይሄም የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል ነው የሚሉት፡፡

የትምህርት መቆራረጥ በደርግ ዘመን በኢሀፓ ትጥቅ ጊዜ ነበር የሚሉት ፕሮፌሰሩ በዛን ወቅት የትውልድ ክፍተት የሚፈጥር አጋጣሚ ነበር፡፡ አኹንም እንደዚያ ዘመን ወይም ከዚያ በበለጠ መልኩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ልጆች ትምህርታቸውን ማግኘት አልቻሉም። ይህ ደግሞ በትውልድ ላይ የሚያሳድረው ጠባሳ ከባድ ነው ብለዋል።

ልጆች በልጅነታቸው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አለባቸው፡፡ እንዲህ አይነት ግጭት በተፈጠረ ጊዜ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አይችሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በልጅነት ዕድሜያቸው የሚሹትን ሳይማሩ ይቀራሉ፡፡ ካደጉ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አብረዋቸው የሚማሩት ሕጻናት ናቸው እና ከእነርሱ ጋር ለመማር ይሸማቀቃሉ፡፡ የሥነ ልቦና ጫናም ይደርስባቸዋል፣ ትምህርቱንም ይተውታል ነው የሚሉት።

በአማራ ክልል የተፈጠረው እጅግ የሚያሳዝን እና ሥነ ልቦናን የሚጎዳ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ በትምህርት ላይ የተፈጠረው መቆራረጥ በትውልድ ላይ ክፍተት ይፈጥራል፤ ወላጆች ሁሉንም ነገራቸውን ለልጆቻው ይሰጣሉ፡፡ ሁሉን ነገር ሰጥተው ያሳደጓቸው ልጆቻቸው ሳይማሩ ሲቀሩ የሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና ከባድ ነው ብለዋል።

በዚህ ወቅት ማስተማር አለመቻል በተማሪ፣ በወላጅ፣ በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በሀገር የሚደርሰው ጉዳት እና የሚፈጠረው ክፍተት የከፋ ነው። በትምህርት ላይ ያለው ችግር ጠባሳው በመጭው ጊዜም አብሮ ይኖራል። የአንድ ወቅት ችግር ኾኖ አይቀርም። ይህ የትውልድ ጉዳይ ነውና ይላሉ።

በትውልድ ላይ ክፍተት ከተፈጠረ በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ አንደኛውን ትውልድ የሚተካው ሌላኛው ትውልድ ነው፡፡ ውጤታማ የኾነ የሀገር ግንባታ እና የትውልድ መተካካት እንዲኖር ለትምህርት ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ያላባሩ ግጭቶች ትውልድን እየጎዱት ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ አለመፍታት ትውልድን እየበደለው ነው፤ ይሄን ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።ሰላምን ለማምጣት፣ ሕዝቡ፣ መንግሥት እና የሌሎች አካላት በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ግጭትን የሚፈጥረው ሰው ነው፣ የሚያስቆመውም ሰው ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ በዚህ ዓለም የምንኖረው አንድ ጊዜ ነው፤ አንድ ጊዜ ለመኖር ደግሞ ለትውልድ እና ለሀገር መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡ በጎነት እና ኢትዮጵያዊ መንፈስ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

መደማመጥ መቻል አለብን፡፡ መደማመጥ ከሌለ እና እልህ ካለ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው ይላሉ፡፡ ሰው ራሱን እየጠየቀ ነው ወይ? ሁሉም እንደሚመለከተው ደረጃ እና መጠን ራሱን እያየ ነው ወይ? ሌላውን ከመጠበቅ ወጥቶ ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ ፕሮፌሰሩ።

ሁሉም ከተጸጸተ እና ካሰበበት መጭውን ትውልድ ማዳን ይቻላል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ መስከን ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ መንገድ ዘግቶ፣ ሰላም ሳይመጣ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አይቻልም። ምክንያቱም በመካከል ሕይወት ማጣት ሊመጣ ይችላልና ይላሉ።

ሁሉም ለሰላም እና ለትውልድ ተሳስሮ ከሠራ የትውልድ መተካካት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ዘመን በሰከነ መንገድ ማሰብን፣ መመካከርን፣ መደማመጥን እና ሀሳብን በነጻነት መግለጽን ይጠይቃል ነው ያሉት። ልጆች እንዲማሩ፣ ወጥተው እንዲገቡ ሁሉም ለሰላም መሥራት አለበትም ብለዋል።

በአፈሙዝ የተዘጋችውን፣ በሰልፍ እና በሰይፍ የተከለከለችውን የዕውቀት በር ለማስከፈት እና ኩራዝ እያበሩ ትምህርትን እየጠበቁ ያሉ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ እርስዎ ምን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይኾን?

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ

Previous articleበደሴ ከተማ በመሠረተ ልማት ላይ ስርቆት የፈጸመ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
Next articleየጤና ባለሙያዎች የጸጥታ ችግር ሳይበግራቸው ማኅበረሰቡ ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ ማድረጋቸውን አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ ገለጹ።