
ደሴ: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር በመሠረተ ልማት ላይ ስርቆት የፈጸመ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ መንበረ ፀሐይ ቀበሌ በግለሰብ ቤት ተከማችተው የተገኙት የመብራት ኀይል፣ የቴሌ፣ የመንገድ አካፋይ ብረቶች እና ሌሎች ቁሳቁስ ናቸው። ከኅብረተሰቡ በደረሠ ጥቆማ ግለሰቡ መያዙን ነው የደሴ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የገለጸው።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አበባው አሻግሬ ሕዝቡ የተሠረቀው ንብረት የራሱ ንብረት መኾኑን አውቆ ጥቆማውን አድርሷል ብለዋል። በቀጣይም ሕዝቡ ወንጀል ተፈጽሞ ሲያይ አስፈላጊውን ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ አካላትን ለሕግ ማቅረብ መቻሉን አስታውሰዋል። ተጠርጣሪው ተገቢውን እና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኝ እንሠራለን ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ ዓሊ ከ15 ቀን በፊት ከኅብረተሰቡ ጋር በተለይም ቆራሊዮ ከሚሠሩ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። ይህ ውጤትም የተገኘው ከምክክሩ በኋላ በቅንጅት መሥራት በመቻሉ ነው ብለዋል።
ከሕዝብ የሚሰወር ነገር የለም ያሉት ኀላፊው ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር አመስግነዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምስራቅ ሪጅን ሴኩሪቲ ማናጀር ኮሎኔል ገዛ አለባቸው በተፈጸመው ስርቆት ሕዝቡ የኔትወርክ ችግር እንዲያጋጥመው አድርጓል ብለዋል። ድርጊቱ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን በተገቢው መንገድ እንዳይሰጡ የሚያደርግ መኾኑን አንስተዋል።
የለሙ ተቋማትን ሕዝቡ መጠበቅ እንዳለበት እና መሪዎችም ይህን ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በኢትዮ ቴሌኮም ላይ የደረሰው ዝርፊያም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሙሐመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን