
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አክብሯል። በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት ላስመዘገቡ ሴቶችም እውቅና ሰጥቷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሴቶች እኩልነት እና ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ ሴቶች ወደ ኀላፊነት እንዲመጡ ኾኗል ነው ያሉት።
“የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የእናቶች ጤንነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል” ብለዋል። በየደረጃ የሚገኙ የጤና ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ከሚጎትቱ ችግሮች ያላቀቀ መኾኑን አንስተዋል።
ቀኑ በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና ለማስወገድ የተደረገውን የትግል እንቅስቃሴ ውጤት የሚዘክር፣ ሴቶች ከነበረባቸው ጭቆና ተላቀው በሁሉም መስኮች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ያደረገ እና የፆታ እኩልነት ያሰፈነ መኾኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም የሴቶችን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል። በዚህም የሴቶች ልማት ኅብረት በማቋቋም ምርት እና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ መደረጉን ነው የገለጹት። ተቋማት የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን