
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ የጎብኝዎች ፍሰት እና ከዘርፉ የተገኘው ገቢ መጨመሩ ተገለጸ። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ በክልሉ የነበረውን ችግር በመቋቋም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ የቱሪስት መስህቦችን የማስተዋወቅ እና የቱሪስቶችን ቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያስቻሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል። ከ16 ሺህ በላይ የውጭ እና ከ5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውን የተናገሩት ኀላፊው ከዚህም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በባሕል እና ቱሪዝም ዘርፉ ለ26 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል። የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን ጥበቃ እና እደሳት መደረጉ ዘርፉ በከፍተኛ ኹኔታ እንዲነቃቃ ማስቻሉን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ የቱሪስት መዳረሻ መሠረተ ልማት እና እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢኒሼቲቪ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውን ተከትሎ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በሁሉም መዳረሻዎቻ መነቃቃትን እያሳየ መኾኑንም አስረድተዋል።
የክልሉን ባሕላዊ እና ታሪካዊ መስህቦች በአግባቡ ማስተዋወቅ በመቻሉ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ112 ሺህ በላይ የውጭ እንዲኹም ከ18 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ ክልሉን ከጎበኙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 30 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም አመላክተዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ በቀጣይም በክልሉ ያሉትን በርካታ የቱሪስት መስህቦች እና መዳረሻዎች በሚፈለገው ልክ አልምቶ ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!