“ልማት ዘላቂ ኾኖ ለትውልድ እንዲሻገር ለማድረግ ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ብዙ ይጠበቃል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

8

ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከዞኖች፣ ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከብሔራዊ ፓርኮች እና ከማኀበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ ጽሕፈት ቤት የዘርፉ መሪዎች ጋር የ2017 ዓ.ም የሰባት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለተከተ በባሕር ዳር ከተማ እየገመገመ ነው።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ልማቶች፣ የኢኮናሚ እና ማኀበራዊ እንቅስቃሴዎች ከአካባቢው ጋር የተዛመዱ እንዲኾኑ የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን እየሠራ ነው ብለዋል።

እየተባባሰ የመጣው የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ምክንያቱ የአጠቃቀም ክፍተት በመኖሩ መኾኑን አንስተዋል። ሀብቱን በአግባቡ ለመጠቀምም ሕግ ወጥቶ እየተተገበረ መኾኑን አንስተዋል። “ልማት ዘላቂ ኾኖ ለትውልድ እንዲሻገር ለማድረግ ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ብዙ ይጠበቃል” ብለዋል።

የአካባቢውን ብዝኃ ሕይዎት በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥሩ መሠራቱን ያነሱት ኀላፊው ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ብሔራዊ ፓርኮች ችግር ደርሶባቸዋል ነው ያሉት። በችግር ውስጥ ኾኖም ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ መድረኩ የተከናወኑ ሥራዎች እየታዩ ቀሪ ተግባራትን እንዴት መፈጸም እንደሚቻል አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ከገጠመው ችግር መሻገር የሚቻለው በሥራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ

Previous article“የታጠቁ ኃይሎች የሕዝብን ሰቆቃ በመረዳት ሰላምን ያስቀድሙ” ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ
Next articleአዲሱ ቻት ጂፒቲ!