“የታጠቁ ኃይሎች የሕዝብን ሰቆቃ በመረዳት ሰላምን ያስቀድሙ” ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ

13

ደብረ ታቦር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የሰላም እና የጸጥታ አደረጃጀቶች ከክልል እና ከዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ክልሉ የሰላም ችግር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም በእስቴ ወረዳ እና አካባቢው ለረጅም ወራት የነበረው የጸጥታ ችግር በሕዝቡ ልማት እና አጠቃላይ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ተገልጿል።

ወረዳው ምንም እንኳን ትርፍ አምራች እና ለግብርና ኢንቨስትመንት ልማት የተመቼ አካባቢ ቢኾንም በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የልማት እንቅስቃሴዎች ችግር ላይ እንደወደቁ በውይይቱ ተነስቷል። በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ መንግሥት በሚያደርገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በዞኑ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው የሰላም ጥሪ ለሕዝቡ ሰላም እና መረጋጋት እንዲኹም ለልማት ሲል መኾኑን ገልጸዋል። የታጠቁ ኃይሎችም መንግሥት የሚያቀርበውን የንግግር እና የሰላም ጥሪ በመቀበል የሕዝቦችን ሰቆቃ ሊያዳምጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርገው ሰላምን መስበክ እና ሕዝብን ማስቀደም ነው ያሉት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊው የታጠቁ ኃይሎች ጦርነት ትውልድን የሚያጎሳቁል እና ልማትን የሚያወድም መኾኑን አውቀው የሰላም አማራጮችን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት
Next article“ልማት ዘላቂ ኾኖ ለትውልድ እንዲሻገር ለማድረግ ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ብዙ ይጠበቃል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)