
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሜጫ ወረዳ ጉቲ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ደርብ አብተው አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት የጀመሩት ከግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ሥልጠና እና ድጋፍ ነው። በሥራው ላይም የተሻሻለ ዝርያ በመጠቀማቸው ውጤታማ እንደኾኑ ነው የነገሩን።
አርሶ አደር ደርብ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን አስታውሰው ይህም በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ እና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። አኹን ላይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርቱን ወደ ውጭ መላክ ባለመቻላቸው ለከተማ ገበያ እያቀረቡ መኾኑንም ተናግረዋል።
ነገር ግን አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎች ያደርጉት የነበረው ድጋፍ እና ምክር መቀዛቀዙንም ገልጸዋል። በመኾኑም ክትትሉን አጠናክረው በመቀጠል፣ የገበያ ትስስሩን በማመቻቸት እና ገበያውን በማረጋጋት ለኅብረተሰቡ የተሻለ ምርት ለማቅረብ እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው በ2017 ዓ.ም በመስኖ ልማት በአዲስ 43 ሺህ 151 ሄክታር እና በነባር 299 ሺህ 329 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 88 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘር መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት። በተለይም በከተማ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ትኩረት ስለመሰጠቱም አብራርተዋል። በመጀመሪያ ዙር 60 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልት ዘር፣ 28 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በፍራፍሬ ዘር መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከዚህም 37 ሚሊዮን ኩንታል አትክልት እና ፍራፍሬ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ምርቱን ከማሳ አያያዝ ጀምሮ ከተመረተ በኋላም ከብክነት በመከላከል ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ ለማቅረብ ለሁሉም የወረዳ ባለሙያዎች የሰብል ጥበቃ እና የድህረ ምርት አያያዝ ሥልጠና ከአንድ ወር በፊት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ከኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የገበያ ትስስሩን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በመጀመሪያው ዙር እስከ አኹን 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልት ምርት ወደ ገበያ መቅረቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ በመጋቢት መጨረሻ አካባቢ የሁለተኛውን ዙር ሽፋን በማሳደግ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን