
ፍኖተ ሰላም: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 29 የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ አስታውቋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማሻሻል በጸጥታ ችግርም ውስጥ ሁኖ መንግሥት ከማኅበረሰቡ እና ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው።
በተለያዩ ወረዳዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 100 አነስተኛ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው። የምዕራብ ጎጃም ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ጊዜው ደግአረገ በበጀት ዓመቱ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ 29 የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፋት ሰባት ወራት በዞኑ በአምስት ወረዳዎች ከ12 ሚሊዮን 564 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በመመደብ ተጨማሪ የመጠጥ ውኃ ተቋማትን ለመገንባት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የኃይል አጠቃቀሙን ከነዳጅ ወደ ፀሐይ ኃይል በመቀየር የውኃ ተቋማትን የብልሽት ምጣኔ እና ወጭ ለመቀነስ እና የተቋማቱን የአገልግሎት ዘመን የማራዘም እና ዘላቂነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም በዞኑ በጃቢ ጠህናን ወረዳ ጓይውብሸት ቀበሌ በተለያየ ምክንያት ለዓመታት ከአገልግሎት ውጭ ኾኖ የቆየውን የውኃ ፕሮጀክት ወደ ሶላር በመቀየር ወደ አገልግሎት በማስገባት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ነው ያሉት። የሺንዲ እና ጅጋ ከተሞች የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማትን ከነዳጅ ወደ ሶላር ኃይል ለመቀየር በጀት እንደተያዘላቸው እና በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረው እና በ37 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እየተገነባ የሚገኘው የጊሽ ዓባይ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሌሎች ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!