
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የላሊበላ፣ ኩልመስክ ፣ ሙጃ የመንገድ ፕሮጀክት እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታውቋል። 48 ነጥብ 78 ኪሎሜትር የሚረዝመው የላሊበላ፣ ኩልመስክ ፣ ሙጃ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ላይ ነው።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የዲዛይን ፣ የአፈር ጠረጋ ፣ የቆረጣ ፣ የሙሌት ፣ የውኃ ማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ የሰብ ቤዝ ሥራዎች እና የድልድይ ግንባታ ጨምሮ እየተከናወነ መኾኑ ተገልጿል። ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ዓለም አቀፉ ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪነግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መኾኑ ተመላክቷል። የማማከሩንና የቁጥጥሩን ሥራ ቤዛ ኢንጅነሪንግ ኬኒያ ሊሚትድ እየሠራው ነው፡፡
የመንገዱ አጠቃላይ የጎን ስፋት በገጠር ከ8 እስከ 10 ሜትር ፣ በቀበሌ 16 ሜትር እና በወረዳ 20 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እንዳለውም ተመላክቷል። ለመንገድ ግንባታው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መመደቡም ተገልጿል።
በአካባቢው በሚስተዋለው ወቅታዊው የጸጥታ ችግር ምክንያት አስፈላጊ የኾኑ የግንባታ ግብዓቶችን፣ ማሽነሪዎችን በበቂ ሁኔታ ለማማጓጓዝ የሥራ ተቋራጩ መቸገሩ ፣ የኮንስትራክሽ ፈንጂ እና የፈንጂ ተቀፅላዎች ማስገባት አለመቻል እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የተካተቱ ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት በግንባታው የሥራ ሂደት ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ቆይተዋል ነው የተባለው።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ከአካባቢው አሥተዳደር እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን ተገልጿል። አሁን ላይ የተሻለ የፕሮጀክት አፈጻጸም የተመዘገበ መኾኑን ያመላከተው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል ተብሏል።
መንገዱ ሲጠናቀቅ በዋናነት የላሊበላ ፣ የኩልመስክ እና የሙጃ ከተሞችን በቅርበት የሚያስተሳስር ነው። ወደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መዳረሻ በመኾን ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ ይኾናልም ተብሏል።
ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በአካባቢው የሚመረቱትን የዘንጋዳ ፣ የገብስ እና ባቄላ ውጤቶች ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ ያፋጥናል ነው የተባለው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!