
ጎንደር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ከሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ጋር የስምንት ወር እቅድ አፈጻጸም በጎንደር ከተማ ገምግሟል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ላቂያው አንዳርጌ በተያዘው ዓመት ከ47 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት 15 ሺህ ለሚኾኑት ሥራ ፈላጊዎች መፍጠር መቻሉን አንስተው በቀሪ ወራት እቅዱን ለማሳካት ይሠራል ብለዋል።
ባለፋት ስምንት ወራት 52 ሚሊዮን ብር ለ106 ኢንተርፕራይዞች ብድር ማቅረብ መቻሉንም ነው የተናገሩት። የሥራ እድል ፈጠራ የሁሉንም ድርሻ የሚጠይቅ መኾኑን የጠቆሙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና ምርትን ማሳደግ አስፈላጊ በመኾኑ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በጎንደር ከተማ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ውስጥ ወጣት ዳውድ ሞላ እና ኪሩቤል አደራጀው የእህል ወፍጮ በማምረት እና በዶሮ እርባታ ሥራ ተደራጅተው መሥራት ከጀመሩ በኋላ በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንደመጣ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል። በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ሥራቸውን ለማስፋት የቦታ ችግራቸው ቢቀረፍ አኹን ካሉበት በተሻለ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን