በ2017/18 የምርት ዘመን ከ47 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት እየሠራ መኾኑን የሰሜን አቸፈር ወረዳ አስታወቀ።

24

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በ2017/18 የምርት ዘመን ከ47 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት እየሠራ መኾኑን የሰሜን አቸፈር ወረዳ አስታውቋል። አርሶ አደር ግዛቸው አዲሱ በሰሜን አቸፈር ወረዳ መስኖ እና መኸርን በመጠቀም በዓመት አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ሰብሎችን እንደሚያመርቱ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የሚያለሙትን ምርት ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ የመግዣ ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት ለመግዛት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርት አምርተን እና ለገበያ አቅርበን የምንሸጥበት ዋጋ ማዳበሪያ ከምንገዛበት ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ነው ያሉት። የሰሜን አቸፈር ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አይሸሽም ላቄ በ2017/18 የምርት ዘመን ከ47 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት እቅድ በመያዝ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል። 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ለእቅዱ መሳካት ከ198 ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሠሩ መኾናቸውም ተናግረዋል። የሰው ሠራሽ አፈር ማዳበሪያ መግዣ ዋጋ መጨመር አርሶ አደሮችን እየፈተነ እንደሚገኝ የተናገሩት ምክትል ኀላፊው አርሶ አደሮች የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው የሚፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት እንዲገዙ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ መልካሙ አለኸኝ በዞኑ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል። የሚቀርበው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በፍትሐዊነት ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት ወራት በእቅድ የተያዘው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ለማድረግ በተለየ ትኩረት ይሠራል ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ከሚፈለገው 18 በመቶ የሚኾነው ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እንደቀረበ የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በሁለት እና ሦስት ወራት ውስጥ ግዥ የተፈጸመባቸው እና በእቅድ የተያዙት ግብዓቶች ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች በቅድሚያ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል። እስካሁን በዞኑ ከ225 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ገብቷል ነው የተባለው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎችን ከግጭት በማውጣት በጋራ ወደ ማልማት ማሸጋገር ተችሏል።
Next articleበሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።