የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎችን ከግጭት በማውጣት በጋራ ወደ ማልማት ማሸጋገር ተችሏል።

17

ከሚሴ: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አጎራባች ወረዳዎች የጋራ የሰላም እና የልማት የምክክር መድረክ በደዋ ጨፋ ወረዳ አካሂደዋል። በመድረኩ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮችን ጨምሮ የሁለቱ ዞኖች ከፍተኛ መሪዎች እና የመከላከያ መኮንኖች ተሳትፈዋል።

የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ነዋሪ ማሞ ዘውድ ለአሚኮ በሰጡት ሃሳብ ሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ሕዝቦች መኾናቸውን ገልጸዋል። አብሮነቱ እንዳይሸረሸር እንደ ሀገር ሽማግሌ እና የሰላም ካውንስል በጋራ ሢሠሩ እንደነበር ተናግረዋል። የደዋ ጨፋ ወረዳ ነዋሪው ሰይድ ሁሴን የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ በጋራ በመገናኘት ሢሠሩ እንደነበር ጠቅሰው በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በጋራ ለመሥራት መግባባት ፈጥረናል ብለዋል።

የደዋ ጨፋ ወረዳ የሰላም ካውንስል አባል ሁሴን ሀሰን የአጎራባች ወረዳዎች በሰላም ካውንስል በኩል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ሲያጠናክሩ እንደነበር ጠቅሰዋል። የሰላም ጥሪ በማድረግ በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድን አባላትም ወደ ሰላም እንዲመጡ እየሠሩ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በቀጠናው ግጭት ለመፍጠር የሚሠሩ አካላት ላይ በተሠራ ተግባር ጸረ ሰላም ኃይሎችን ከሕዝቡ መነጠል ተችሏል ብለዋል። በቀጣይም ተፈናቅለው ወደቀያቸው ያልተመለሱ አካላትን ወደቀያቸው ለመመለስ በጋራ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ ባለፈው አንድ ዓመት በተከታታይ በተሠራው ሥራ ቀጠናውን ከግጭት በማውጣት በጋራ ወደ ማልማት ማሸጋገር ተችሏል ነው ያሉት። የተጀመረውን የሰላም እና የልማት እንቅስቃሴ ዘላቂ ለማድረግም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶች የመብት ጥሰትን ለመከላከል እና ሁለንተናዊ ተሳትፎአቸውን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም ይገባል።
Next articleበ2017/18 የምርት ዘመን ከ47 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት እየሠራ መኾኑን የሰሜን አቸፈር ወረዳ አስታወቀ።