የሴቶች የመብት ጥሰትን ለመከላከል እና ሁለንተናዊ ተሳትፎአቸውን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም ይገባል።

13

ደባርቅ: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሻሻል የአፈጻጸም ብቃታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ በደባርቅ ከተማ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሴቶች ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሴቶች ዕውቅና እና ማበረታቻ ሽልማት የመስጠት መርሐ ግብር አካሂዷል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መኾን የቻሉት ወይዘሮ እናንየ መስፍን በርካታ ችግሮች ቢኖሩም በይቻላል መንፈስ እና በትጋት ከሠሩ የማይደረስበት የስኬት ጫፍ እንደሌለ ተናግረዋል።

ሴትነት ከፍተኛ ቤተሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ኀላፊነትን የመወጣት ብቃት የሚጠይቅ እንደኾነም ገልጸዋል። በዕለቱ በላቀ አፈጻጸም ተሸላሚ የኾኑት መምህርት ነኢማ ዘውዱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሻሻል የአፈጻጸም ብቃታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ መልካሙ ሴቶች በጦርነት እና በሌሎችም ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ መኾናቸውን ተናግረዋል። የሴቶች የመብት ጥሰትን ለመከላከል እና ሁለንተናዊ ተሳትፎአቸውን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም እንደሚገባም አንስተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አስራት ይበይን የሴቶችን የመብት ጥሰት ለመከላከል እና ሲከሰቱም አፋጣኝ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ለማስቻል መዋቅሮች እና የሴት አደረጃጀቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የተገኙ ለውጦችን እና መሻሻሎችን ለማስቀጠል፣ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ሴቶች ቁርጠኛ ሊኾኑ እንደሚገባም አንስተዋል።

ሴቶች በሌማት ትሩፋት እና በግብርናው ዘርፍ ያሳዩት የላቀ አፈጻጸም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የከተማ ግብርና የሴቶችን ተጠቃሚነት እያሳደገ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎችን ከግጭት በማውጣት በጋራ ወደ ማልማት ማሸጋገር ተችሏል።